በጋምቤላ ከተማ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ተነሳ

ታትሟል

በጋምቤላ ክልል ከአንድ ሳምንት በፊት ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ መነሳቱን  የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊው ኡጉቱ አዲንግ በሰጡት መግለጫ በክልሉ መረጋጋት በመታየቱ ተጥሎ የነበረው ጊዜያዊ የሰዓት እላፊ ገደብ ተነስቷል ብለዋል።

በሰዓት እላፊው ምክንያት ከአንቡላንስና ከጸጥታ ኃይሎች ተሽከርካሪዎች ውጭ ባለ ሦስት እግርን ጨምሮ ተሽከርካሪዎች በመታገዳቸው ሕብረተሰቡ ለችግር ሲዳረግ ቆይቶ እንደነበርም ኃላፊው ተናግረዋል።

አሁን ላይ በከተማው በቂ የጸጥታ ኃይል በመኖሩና አንጻራዊ ሰላም በመታየቱ በጊዜያዊነት ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ መነሳቱን አጉቱ በመግለጫቸው አስረድተዋል።

ከቀናት በፊት የሰዓት እላፊውን የተጣለው በጋምቤላ ከተማ ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ “ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር” መሆኑን የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቆ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ ውስጥ ከአምቡላንሶች እና ከፀጥታ ኃይሎች ተሽከርካሪዎች በስተቀር፣ ማንኛውም የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11፡30 ድረስ ገደብ ተጥሎባቸዋል ቆይቷል።

ከአንድ ወር በፊት ሰኔ 07/2014 ዓ.ም በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ለሰዓታት የከተማዋን የተወሰነ ክፍል ተቆጣጥረው ነበር።

በወቅቱም የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ታጣቂዎቹን ከከተማዋ ማስወጣት የቻሉ ሲሆን፣ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

ይህንን ጥቃት ተከትሎም በዚያው ሰሞን በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አማካይነት የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለመቆጣጠር የምሽት የእንቅስቃሴ ገደብ ቢጣልም፣ ቁጥጥሩ የላላ እንደነበረ አቶ ኡገቱ አመልክተው ነበር።

አቶ ኡጉቱ የሰዓት እላፊው መነሳቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ከተማዋ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ገልጸው፤ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ያልተለመደ ነገር ሲመለከት ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

ባለፈው ሳምንት ከሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ጀምሮ የጋምቤላ ክልል አጎራባች የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በዋና ከተማው አሶሳ በተመሳሳይ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።