ኢትዮጵያውያን በእስያ የሚገኙ የሳይበር አጭበርባሪዎች ተጠቂ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስጠነቀቀ

ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን ሥራ ፈላጊዎች በእስያ አገራት ውስጥ በስፋት የሚገኙ የማጭበርበሪያ ካምፖች ተጠቂ መሆናቸው በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የመንግሥታቱ ድርጅት አስጠነቀቀ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ (አይኦኤም) የወንጀል መረቦች ከአገር ውጪ ሥራ የሚፈልጉ ሰዎችን በመመልመል፣ ጥብቅ ጥበቃ በሚደረግላቸው ካምፖች ውስጥ በማስፈራራት፣ ድብደባ እና ስቃይ በመፈጸም የሳይበር ማጭበርበር እንዲፈጽሙ ያደርጓቸዋል ብሏል።
ረቡዕ ዕለት ከሚከበረው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከያ ዓለም አቀፍ ቀን ዋዜማ አይኦኤም ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ በመላው እስያ ከሚገኙ የማጭበርበሪያ ማዕከላት እንዲወጡ ከተደረጉ ሰዎች መካከል ከምሥራቅ አፍሪካ የመጡት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።
ድርጅቱ ይህንን አዲስ ብቅ ያለ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መንገድ ነው ሲል ሁኔታውን ገልጾታል።
ተጎጂዎች ብዙውን ጊዜ በውጭ አገር ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን እንደሚያገኙ በሚገልጹ ማስታወቂያዎች አማካኝነት ይሳባሉ።
ይሁን እንጂ ወደታለመላቸው ሥፍራ ሲደርሱ ፓስፖርታቸው ይወሰድባቸዋል፤ እንዲሁም በቋሚ ክትትል ስር ሆነው በኦንላይን የማጭበርበር ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ይገደዳሉ።
የመንግሥታቱ ድርጅት እንደገለጸው አንዳንድ ከካምፖቹ እንዲወጡ የተደረጉ ሰዎች በማጭበርበር ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ድብደባ፣ ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸምባቸው፣ ለረሃብ መዳረጋቸው እና ብቻቸውን መታሰራቸውን ተናግረዋል።
"ምሥራቅ አፍሪካውያን በማጭበርበሪያ ካምፖች ውስጥ መገኘታቸው ለግዳጅ ወንጀል ሰዎችን ማዘዋወር ከአሁን በኋላ የሩቅ ስጋት እንዳልሆነ ያሳያል" ሲሉ የአይኦኤም የምሥራቅ፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ፍራንትዝ ሴሌስቲን ተናግረዋል።
"የወንጀል ቡድኖች በቀጣናችን የሚገኙ ሥራ ፈላጊዎችን ባሕር ማዶ ሥራ ይገኛል በሚል በሐሰተኛ ማባበያ ያጠምዳሉ።"
አይኦኤም እንደገለጸው፣ የሰዎች ዝውውር አደራጅ ቡድኖች እንቅስቃሴያቸውን ከአስያ ውጭ እያሰፉ ሲሄዱ ከአፍሪካ የሚመለምሏቸው ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
ከአውሮፓውያኑ 2022 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ኤጀንሲው በደቡብ ምሥራቅ እስያ ለግዳጅ ወንጀል ተግባር ከተወሰዱት ከ39 አገራት ለመጡ ከ3,500 በላይ ሰዎች ድጋፍ አድርጓል። ከእነዚህ መካከል ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከሕንድ፣ ከስሪላንካ፣ ከባንግላዴሽ የመጡ ተጎጂዎች ይገኙበታል።
አይኦኤም የኢትዮጵያውያኑ እና የኬንያውያኑ ቁጥር ምን ያህል አንደሆነ አላሳወቀም።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ከሆነ፣ በምሥራቅ እስያ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ የሚከናወኑ የኦንላይን የማጭበርበር ተግባራት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ88 እስከ 114 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ገቢ አስገኝተዋል።
እንዲሁም ለሕገወጥ ሰው ዝውውር የተዳረጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች በእነዚህ የማጭበርበር ማዕከላት ውስጥ ታጉረው እንደሚገኙ ይታመናል።
እንደ ምያንማር፣ ካምቦዲያ እና ላኦስ ባሉ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት የተስፋፉት እነዚህ ካምፖች በየዓመቱ "በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ የሚገኝባቸው" የኦንላይን ማጭበርበሪያ ናቸው።
ሕገ ወጥ የሰዎች እና ሕጻናት ዝውውር፣ የግዳጅ ወንጀለኝነት፣ የሰዎች ስቃይ፣ ሕገ ወጥ ቁማር እንዲሁም በወንጀል የተገኘን ሀብትን ሕጋዊ ማስመሰል የእነዚህ ካምፖች መገለጫ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
አይኦኤም እንደገለጸው በኦንላይን የማጭበርበር ተግባራት ውስጥ እንዲሳተፉ የተገደዱ ብዙ ተጎጂዎች በስህተት እንደ ወንጀለኛ ይቆጠራሉ።
ኤጀንሲው መንግሥታት እነዚህን ሰዎች ክስ ሊመሠረትባቸው የሚገባ ወንጀለኞች አድርገው ከመመልከት ይልቅ፣ ጥበቃና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ተጎጂዎች አድርገው እንዲመለከቷቸው አሳስቧል።
በተጨማሪም አይኦኤም፣ ሥራ ፈላጊዎች ከአገር ውጭ የሚቀርቡላቸውን የሥራ ዕድሎች በጥንቃቄ እንዲያጣሩ፤ እንዲሁም ያልተለመደ ከፍተኛ ደመወዝ፣ ፈጣን የሥራ ምደባ ወይም እውነት ለመሆን የማይችሉ እጅግ ማራኪ የሆኑ ዕድሎችን ቃል በሚገቡ አሠሪዎች ወይም አገናኞች ሲቀርቡላቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ዩናይትድ ስቴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፒስ የተሰኘው የአሜሪካ መንግሥት የባለሙያዎች ቡድን የበርማ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ጄሰን ታወር በአንድ ወቅት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእነዚህ ካምፖች መነሻቸው የቻይና ሕገ ወጥ ቁማር ኩባንያዎች ናቸው።
የቻይና መንግሥት በእነዚህ አቋማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ የወንጀል ቡድኖቹ አጎራባች ወደሆኑት ፊሊፒንስ፣ ካምቦዲያ እና ምያንማር በመሻገር ተመሳሳይ ተግባር መፈጸም መቀጠላቸውን ጄሰን ያስረዳሉ።
ጄሰን እንደሚገልጹት የወንጀል ቡድኖቹ ዋነኛ ዓላማ ቻይናውያን ዜጎችን በተለያዩ መንገዶች በማታለል ቁማር ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ ገንዘብ መሰብሰብ ነበር። የቻይና እርምጃን ተከትሎ ግን ፊታቸውን ወደ ሌሎች አገራት ዜጎች እና አዲስ የበይነ መረብ ማጭበርበር ዘዴዎችን ወደ መጠቀም አዞሩ።
ጄሰን፤ "[በዚህ ወቅት] የግዳጅ ሠራተኞችን መጠቀም ጀመሩ። ለዚህም መጀመሪያ ላይ ሰዎችን ማገት ያዙ። 2021 አካባቢ ካምቦዲያ ውስጥ የሰዎች የመታገት ታሪኮች ይሰሙ ነበር። [የግዳጅ ሠራተኛ የሚሆኑት] በመጀመሪያ ቻይናውያን ነበሩ፤ ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስፋፉት" ሲሉ የተስተዋለውን ለውጥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኮቪድ ምክንያት ታግደው የነበሩ በረራዎች በድጋሚ ሲጀመሩ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ሰዎች መመልመል መጀመራቸውን ያስረዳሉ።
"ዘመናዊ ባርነትን" ለመዋጋት የሚሠራው የዩናይትድ ኪንግደም ተቋም ያደራጀው በተለያዩ አገራት የሚገኙ የማጭበርበሪያ ካምፖች ዝርዝር እንደሚያሳየው ምያንማር ውስጥ ይህ ተግባር የሚፈጸምባቸው ቢያንስ 154 ግቢዎች አሉ።
የካምፖቹ ዝርዝር እንደሚያሳየው ከሌሎች አገራት ይበልጥ ምያንማር ውስጥ ብዛት ያላቸው ካምፖች ይገኛሉ። የካምፖቹ ባለቤቶች ሕንጻዎችን የማጭበርበር ድርጊት ለሚያከናውኑ የወንጀል ቡድኖች ያከራያሉ።















