ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርሱ ወደ ቢዮንሴ ኮንሰርት እንዳይገቡ ፍተሻ መደረጉ ተገለጸ
የሰዎችን ምሥል በማየት ማንነታቸውን የሚገልጸውን የፌሻል ሪኮግኒሽን በመጠቀም ወደ ቢዮንሴ ኮንሰርት የሚገቡ ሰዎች ሕጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙ ወይም አሸባሪ መሆናቸው እየተለየ እንደነበር ተገለጸ።
ኮንሰርቱ የተካሄደው በዌልስ በሚገኘው ካርዲፍ ከተማ ነበር።
እአአ በ2017 በማንችስተር አሬና ከደረሰው የቦንብ ፍንዳታ በኋላ አሸባሪዎችን በኮንሰርቶች ወይም ሌሎች ሰው የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች መፈለግ እየተለመደ መምጣቱን የደቡብ ዌልስ የፖሊስ ኮሚሽነር አሉን ማይክል ተናግረዋል።
ኮንሰርቱን የሚታደሙ በርካታ ሴት ሕጻናት ስላሉ ሕጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎችን ለመለየት እንደሞከሩም አክለዋል።
ኮሚሽነሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ካሜራ ተጠቅሞ በአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ሰዎችን መለየት ያለውን አስፈላጊነት ገልጸዋል።
ቢዮንሴ በካርዲፍ ኮንሰርት ባዘጋጀችበት ወቅት የሰዎች ምሥል እየታየ በወንጀል ተፈላጊ የሆኑ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ካለ እየተነጻጸረ ነበር።
ይህንን ካሜራ መጠቀምን በተመለከተ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ቅሬታ አላቸው።
“መድልዎ ያስከትላሉ። የሰዎችን ግላዊ መረጃ ጥበቃ ይጥሳሉ” ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ጠበቃ ኬቲ ዋትስ ተናግረዋል።
የፖሊስ ኮሚሽነሩ በበኩላቸው “የሁሉንም ፎቶ አንስተን አናስቀምጥም። ፎቷቸው የሚቀመጠው በሚፈለጉ ወንጀለኞች ዝርዝር ያሉት ብቻ ናቸው” ይላሉ።
እአአ ግንቦት 17 በተደረገው በቢዮንሴ ኮንሰርት ላይ ፌሻል ሪኮግኒሽን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻል እንደታየም አክለዋል።
“በአክራሪነት ወይም አሸባሪነት የሚታወቁ ሰዎች እንዲሁም ሕጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች ወደ ኮንሰርቱ እንዳይገቡ ነው የተደረገው” ብለዋል።