ኢራን በወታደራዊ ተቋም ላይ የተቃጣብኝን የድሮን ጥቃት አከሸፍኩ አለች

ታትሟል

የኢራን መከላከያ ሚኒስቴር ኢሰፋሃን ተብሎ በሚጠራው ከተማ በሚገኝ ወታደራዊ ተቋም ላይ የተቃጣ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አከሸፍኩ አለ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጥቃቱ ሦስት ድሮኖች ተሳትፎ ያደረጉ ቢሆንም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል።

አንደ ሰው አልባ አውሮፕላን በአየር መቃወሚያ ሲወድም ሁለቱ ደግሞ ‘በመከላከያ ወጥመድ’ በሕንጻዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶ ተይዘዋል ብሏል የኢራን መንግሥት።

ኢራን አክሽፌዋለሁ ስላለችው ጥቃት ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።

በኢራን ላይ ተሞክሯል ስለተባለው ጥቃትም እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

ኢራንም ለጥቃቱ ተጠያቂ ነው ያለችው አካል የለም። 

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሁሴን አሚር-አብዶላሂአን የዚህ ‘የፈሪ ጥቃት’ ዓላማ አገሪቱ እንዳትረጋጋ ለማድረግ ያለመ ነበር ብለዋል።

ሚንስትሩ ይህ ሙከራ ኢራን ሰላማዊ የኒውክለር ኃይል ለማበልጸግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚጎዳ አይደለም ብለዋል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ፓትሪክ ራይደር በዚህ ጥቃት የአሜሪካ ጦር ምንም አይነት ተሳትፎ አለማድረጉን ስለመናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ኢራን በጦር ተቋም ላይ የድሮን ጥቃት ተቃጣብኝ ያለችው በኒውክሌር ፕሮግራሟ እና ለሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን እያቀረበች ነው በሚል ከምዕራባውያን ጋር አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ነው።

አገሪቱ በቅርብ ሳምንታትም በአገር ውስጥ ተቃውሞ መረጋጋት ርቋት ቆይታለች።

ለኢራን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በተላከው መግለጫ የአገር መከላከያ ሚኒስቴሩ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቱ የተፈጸመው በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ቅዳሜ ጥር 20/2015 ዓ.ም. እኩለ ለሊት ላይ መሆኑን ገልጿል።

የኢራን የዜና ወኪል የጥቃቱ ዒላማ የነበረው የጥይት ማምረቻ ተቋም ነው ሲል ዘግቧል።

ኢንፋንህን ግዛት በርካታ ግዙፍ የአየር ኃይል ጦር ሰፈሮች እና የኒውክሌር ማብለያ ጣቢያ ስፍራዎች መገኛ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢራን የጦር ተቋማት፣ የኒክሌር ማብሊያ ጣቢያዎች እና የኢንዱስትሪ ተቋማት ላይ ፍንዳታዎች፣ የእሳት አደጋ እና የሳይበር ጥቃቶች እያጋጠሙ ነው።

እአአ 2021 ላይ ኢራን በቁልፍ የኒውክሌር ማብሊያ ጣቢያ ላይ ጉዳት አድርሳብኛለች ስትል እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋ ነበር።

እአአ 2020 ላይ ደግሞ ለኢራኑ የኒውክለር ከፍተኛ ተመራማሪ ሞሐሰን ፋክህሪዛዴህ ግድያ ቴህራን እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋ ነበር።