ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፖሊስ ድብደባ የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ቤተሰቦች በፖሊስ ደንብ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠየቁ
ታየር ኒኮልስ የተባለ የ29 ዓመት አፍሪካ-አሜሪካዊ በአሰቃቂ ሁኔታ በፖሊስ ሲደበደብ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምሥል መውጣቱን ተከትሎ ቤተሰቦቹ በፖሊስ መዋቅር ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠየቁ።
በቴነሲ ግዛት ሜምፈስ ከተማ የተፈጸመው ይህ የፖሊሶች ቅጥ ያጣ እርምጃ በመላው አሜሪካ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱ ይታወቃል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተንቀሳቃሽ ምሥሉ “ሕሊናን የሚያውክ፤ የአሜሪካንን ምሥል የሚያጠለሽ” ብለውታል።
የታየር ኒኮልስ ቤተሰብን የወከሉት ጠበቃ የአሜሪካ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት የፖሊሶች መዋቅርና አሰራር ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ኒኮላስ በአምስት ፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመበት ባለፈው ጥር ወር ነበር።
ድብደባው ሲፈጸምበት እናቴ ድረሽልኝ እያለ ሲጮኽ ይሰማል።
ኒኮላስ ከድብደባው በኋላ ሆስፒታል ጽኑ የህሙማን ክፍል ገብቶ የቅርብ ክትትል እየተደረገለት ቢቆይም ከሦስት ቀናት በኋላ ሕይወቱ አልፋለች።
የቤተሰቡ ጠበቃ ለጆ ባይደን ባስተላለፉት መልእክት የጆርጅ ፍሎይድ ፖሊሲንግ አክት የሚባለውን ረቂቅ የበለጠ ድጋፍ እንዲያገኝ የታየር ኒኮልስን ድብደባና ሞት እንደ አስረጅ እንዲጠቀሙበት ተማጽነዋል።
በአሜሪካ የፖሊስ ስምሪት፣ አወቃቀርና ደንብ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ መቅረብ የጀመረው በተለይ ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ ጉሮሮውን ተጭኖት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱን ማጣቱን ተከትሎ ነበር።
የጆርጅ ፍሎይድ ሞት ከአሜሪካ አልፎ በአውሮፓም ጭምር አብዮት ያክል ንቅናቄ መፍጠሩ አይዘነጋም።
የጆርጅ ፍሎይድ ጀስቲስ አክት የሚል ስም ያለው ረቂቅ በፈረንጆቹ በ2021 ነበር የተዋወቀው።
ይህ ረቂቅ በፌዴራል ደረጃ ፖሊሶች ተጠርጣሪ ላይ ጎሮሮውን ቆልፎ የመያዝ ተግባርን የሚከለክል ነው።
ከዚህም ሌላ ፖሊሶች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠርጣሪዎች ላይ ሲፈጽሙ የሚከሰሱበት ሁኔታና ሂደትን ቀላል ያደርጋል።
ይህ ረቂቅ በሕግ መምሪያው ምክር ቤት በከፍተኛ ድምጽ አልፎ ነበር። ይሁንና የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ረቂቁን በይደር አቆይቶታል።
ያን ጊዜ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት በዲሞክራቶች የበላይነት የተያዘ ስለነበረ ነው ረቂቁ ማለፍ ችሎ የነበረው።
አሁን ሪፐብሊካን መጠነኛ ብልጫ በምክር ቤቱ ስላላቸው ተመሳሳይ ረቂቅ ሕጎች የማለፍ እድላቸው የተመናመነ ነው።
የሟቹ ኒኮልስ ጠበቃ እንደተናገሩት “የወንድማችንን ሞት ይህን የጆርጅ ፍሎይድን ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ካላስቻለን በራሳችን ልናፍር ይገባል።”
ጠበቃው ጨምረውም በፖሊስ ላይ ማሻሻያ ካልተደረገ የጥቁሮች ሞት ይቀጥላል።
ዴሪክ ጆንሰን የተባሉ ሌላ የመብት ተቆርቋሪ በበኩላቸው ረቂቅ ሕጉን ባለማጽደቅ ሌላ የሕልፈት ዜና እየጻፍን መሆኑን መረዳት አለብን ብለዋል።
ሟች ኒኮልስ ብላክ ላይቭስ ማተር ለሚለው ንቅናቄ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጥ ሰው እንደነበር የልጅነት ጓደኛው ለቢቢሲ ተናግራለች።
ኒኮልስን ለሞት የዳረጉት አምስቱ ፖሊሶች ከሥራ ተባረዋል።
ይሁንና ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ አራቱ በዋስ ተለቀዋል።