ትራምፕ የአሜሪካን የኒውክሌር ሚስጥሮች የያዙ ሰነዶች መውሰዳቸው ተጠቆመ

ትራምፕ ወስደውታል የተባለው ሰነድ

የፎቶው ባለመብት, DOJ

ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገራቸውን የኒውክሌር ሚስጥሮችን እና ወታደራዊ እቅዶችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን አላግባብ በመያዝ ክስ ቀረበባቸው።

በትራምፕ ላይ በቀረበባቸው 37 ክሶች መሰረት ትራምፕ እነዚህን ሰነዶች በፍሎሪዳ በሚገኘው ቤታቸው መታጠቢያ ክፍሎች አስቀምጠዋል እንዲሁም ለመርማሪዎች ሃሰት ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሰነዶቹ አያያዝ ላይ የሚደረገውን ምርምራ ለማደናቀፍ ሞክረዋል ይላል ክሱ።

በአውሮፓውያኑ 2024 በሚደረገው የፕሬዚዳንትነት ምርጫ እወዳደራለሁ ያሉት ትራምፕ “ምንም አይነት ጥፋት አልፈጸምኩም” ሲሉም አስተባብለዋል።

ክሱ በሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በግል ረዳታቸው ዋልት ናውታም ላይ ነው።

የቀድሞ የዋይት ሃውስ ወታደራዊ ዝግጅት አስተናባሪ የነበሩት ረዳታቸው ከአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ሰነዶችን ለመደበቅ ሞክረዋል የሚልም ክስ ቀርቦባቸዋል።

49 ገጾችን የያዘው ይህ ቅስ በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀረበ የተባለውንም የፌደራል ክስ ይዟል።

ትራምፕ በግላቸው ይዘውታል የተባሉት ሚስጥራዊ ሰነዶች፦

  • የአሜሪካ የኒውክሌር ፕሮግራሞች
  • የአሜሪካ እና የውጭ አገራት የጦር መሳሪያዎችና የመከላከያ አቅም
  • አሜሪካ እና አጋሮቿ በወታደራዊ ጥቃቶች ሊኖራቸው የሚችል ተጋላጭነት
  • ለውጭ ጥቃት ምላሽ ሊሆን የሚችል አጸፋዊ ምላሽ እቅዶችን አካቷል።

ትራምፕ ስልጣናቸውን ሲለቁ ወደ 300 የሚጠጉ ሚስጥራዊ ፋይሎችን በፓልም ቢች ወደሚገኘው ማር አ ላጎ ወደተሰኘው ቤታቸው መውሰዳቸውን አቃብያነ ህግ ተናግረዋል።

በውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኘው ይህ ቤታቸው ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ክበብ መሆኑም ተነግሯል።

በዚህ ቤታቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት እና እንግዶች የተስተናገዱበት ሲሆን በአንደኛው አዳራሽም እነዚህ ሚስጥራዊ ሰነዶች እንደተገኙም ክሱ ጠቅሷል።

ትራምፕ እነዚህን ደብዛቸው ጠፍቷል የተባሉ ሰነዶችን ጠበቃቸው “ደብቀዋቸዋል ወይም አጥፍተዋቸዋል” በሚልም የኤፍቢአይን ምርመራ ለማደናቀፍ መሞከራቸውንም አቃብያነ ህጉ በተጨማሪ አስረድተዋል።

“እዚህ ምንም የለም ብለን ብንነግራቸው አይሻልም ወይ?” ብለው ትራምፕ ለአንዱ ጠበቃቸው አስተያየታቸውን እንደሰጡ በክሱ ላይ ተመላክቷል።