አውስትራሊያ ምዕራብ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርጋ እውቅና የሰጠችበትን ውሳኔ ቀለበሰች

ታትሟል

አውስትራሊያ ምዕራብ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ እንደሆነች ከአራት ዓመታት በፊት ያሳለፈችውን ውሳኔ ቀልብሳለች።

ካንቤራ እአአ በ2018 ኣሳለፈችው ውሳኔ የሠላም ስምምነትን የሚጋፋ እና አውስትራሊያ ከሌሎች ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ፔኒ ዎንግ ገልጸዋል።

አውስትራሊያ የእስራኤል “ጽኑ ወዳጅ” ሆና እንድምትቆይም አበክረው ገልጸዋል። ኤምባሲያቸው በቴል አቪቭ እንደሚቆይ ጠቁመዋል።

በእስራኤል እና በፍልስጥኤማውያን መካከል በጣም አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የኢየሩሳሌም ባለቤትነት ነው።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ “ይህ ውሳኔ በመገናኛ ብዙሃን የተሳሳተ ዘገባ በአውስትራሊያ ከተወሰደው የችኮላ ምላሽ አንጻር የአውስትራሊያ መንግሥት ሌሎች ጉዳዮችን በቁም ነገር እና በሙያዊ መንገድ ብቻ እንደሚያካሄድ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

"ኢየሩሳሌም የዘላለማዊ እና የተዋሃደችው እስራኤል ዋና ከተማ ናት። ይህንን ምንም ነገር አይለውጠውም።" ብለዋል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሃገራቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመቀልበስ በ2017 ጥንታዊቷን ከተማ የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው ዕውቅና በመስጠታቸው ዓለም አቀፍ ትችት አስተናግደዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲም ከቴላቪቭ ወደ እየሩሳሌም በግንቦት 2018 ተዛውሯል።

ከወራት በኋላ የወቅቱ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን መንግሥታቸውም ለምዕራብ እየሩሳሌም እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸው ኤምባሲያቸውን ግን ከቴልአቪቭ እንደማያዛውሩ ተናግረው ነበር።

በግንቦት ወር በተካሄደ ምርጫ የሞሪሰን መንግስት ስልጣኑን አጥቷል።

ማክሰኞ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ የቀድሞው መንግስት በአውስትራሊያ ከሚካሄደው ምርጫ በፊት የአይሁድ መራጮችን ድምፍ ለማግኘት ወሰደ ያሉትን ውሳኔ “አስቂኝ ጨዋታ” ብለውታል።

"ሞሪሰን በፖለቲካ ለመጫወት በመወሰን የአውስትራሊያን ቦታ በመቀያየራቸው አዝኛለሁ። እነዚህ ለውጦች በአውስትራሊያ ማህበረሰብ ውስጥ ለዚህ ጉዳይ በጥልቅ የሚጨነቁ ብዙ ሰዎች ፈጥሯል” ብለዋል።

የእየሩሳሌም ሁኔታ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም ህዝብ መካከል የሚካሄደው የሠላም ድርድር አካል ሆኖ እንዲፈታ ሃገራቸው “የቀድሞ እና የቆየ” አቋም መቀጠሉን አረጋግጠዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ለማዛወር እያሰበች ነው። ከአሜሪካ በተጨማሪ ሆንዱራስ፣ ጓቲማላ እና ኮሶቮ በእሩሳሌም ኤምባሲዎች ያላቸው ሃገራት ናቸው።

እስራኤል እየሩሳሌምን "ዘላለማዊ እና ያልተከፋፈለች" ዋና ከተማዬ ስትል ትገልጻለች። ፍልስጤማውያን በበኩላቸው በ1967 የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በእስራኤል የተወሰደባቸውን ምስራቅ እየሩሳሌምን የወደፊቷ ሃገራቸው ዋና ከተማ አድርገው ይቆጥራሉ።

የእየሩሳሌም ጉዳይ አንደኛው የእስራኤል እና የፍልስጤም የግጭት ምክንያት ነው።

እስራኤል በኢየሩሳሌም ላይ የምታነሳው ሉዓላዊነት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ አያውቅም። በ1993ቱ የእስራኤል እና የፍልስጤም የሠላም ስምምነት መሠረት የኢየሩሳሌም ጉዳይ ወደፊት በሚደረጉ የሠላም ንግግሮች የሚታይ ይሆናል።