ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፓሪስ አውሮፕላን ማረፊያ ለ18 ዓመታት የኖረው ግለሰብ አረፈ
በፓሪስ አውሮፕላን ማረፊያ ለ18 አመታት የኖረው ኢራናዊ አረፈ።
በዲፕሎማሲያዊ ችግሮች ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የነበረው ሜህራን ካሪሚ ናሴሪ በአውሮፓውያኑ 1988 የቻርለስ ደጎል አየር ማረፊያን ቤቱ ያደረገው ።
በህይወቱም የሚያጠነጥን ‘ዘ ተርሚናል’ የተሰኘ ፊልም በአውሮፓውያኑ 2004 ተሰርቷል።
በፊልሙም ላይ ቶም ሃንክስ ተውኗል።
ሜህራን በመጨረሻም በፈረንሳይ የመኖር መብቱ ቢረጋገጥለትም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ተመልሶ በዚያው ቤቱን እንዳደረገ ህይወቱ ማለፉን አንድ የአየር ማረፊያ ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ 1945 በኢራን ክውዜስታን ግዛት የተወለደው ሜህራን ወደ አውሮፓም ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው እናቱን ፍለጋ ነበር።
ትክክለኛ የጉዞ ሰነድ የለውም በሚል ከዩኬ፣ ኔዘርላንድስ እና ጀርመንም ተባርሮ በቤልጂየም ውስጥ ጥቂት አመታትን አሳልፏል።
ከዚያም ወደ ፈረንሳይ ሄዶ የአየር ማረፊያውን 2ኤፍ ተርሚናል ቤቱን አደረገ።
አግዳሚ ወንበርም ላይ ጎጆውን ቀልሶ ያከማቸውን ንብረቶች በጋሪ ውስጥ አድርጎ ጊዜውን የህይወት ታሪኩን በመጻፍና፣ መጽሃፍ እና ጋዜጦችንም በማንበብ ሲያሳልፍ ነበር።
ታሪኩ የአለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን በተጨማሪም የታዋቂውን ፊልም ዳይሬክተር ስቴቨን ስፒልበርግም ቀልብንም ያዘ።
በህይወቱ ላይ የሚያጠነጥነውና ቶም ሃንክስ ካትሪን ዜታ ጆንስ የሚተውኑበት ‘ዘ ተርሚናል’ የተሰኘ ፊልምም ተሰራ።
ፊልሙ ከወጣ በኋላ ጋዜጠኞች ለዚህ የሆሊውድ ፊልም መነሻ የሆነውን ሰውም ለማነጋገር መትመም ጀመሩ።
በአንድ ወቅት እራሱን "ሰር አልፍሬድ" ብሎ ይጠራ የነበረው ሜህራን በቀን እስከ 6 ቃለመጠይቆችን ያደርግ እንደነበር ለ ፓሪዚየን ዘግቧል።
ምንም እንኳን በስደተኝነት በፈረንሳይ እንዲቆይ በአውሮፓውያኑ 1999 ፈቃድ ቢሰጠውም እስከ አውሮፓውያኑ 2006 ድረስ በአየር ማረፊያው ይኖር ነበር።
በመጨረሻም በህመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ከፊልሙ በተቀበለው ገቢ ሆስቴል ውስጥ ይኖር እንደነበር ሊበሬሽን የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል።
ሜህራን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ተመልሶ እስካረፈበት እለት ድረስ ይኖር እንደነበር የአየር ማረፊያ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ አክለውም በብዙ ሺዎች ዩሮዎች በእጁ ይዞ እንደተገኘም ተናግረዋል።