ተቀናቃኝ ቡድኑን በድሮን የሰለለው የካናዳ የኦሊምፒክ ቡድን ጠንካራ ቅጣት ተላለፈበት

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የካናዳ የሴቶች የኦሊምፒክ ቡድን ተጋጣሚ ቡድንን በሰው አልባ አውሮፕላን መሰላሉን ተከትሎ የነጥብ እና የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም የአሰልጣኝ እግድ ተላለፈበት።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ እና የካናዳ የእግር ኳስ ማኅበር ያደረጉትን ምርመራ ተከትሎ የካናዳ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጋጣሚው የኒው ዚላንድ ቡድን በልልምድ ላይ ሳለ በድሮን ሰልሏል ብለዋል።

ይህን ተከትሎ ቡድኑ የስድስት ነጥብ ቅጣት የተላለፈበት ሲሆን፤ የኦሊምፒክ ቡድኑ አሰልጣኝ ለአንድ ዓመት ታግደው የካናዳ የእግር ኳስ ማኅበር 175 ሺህ ፓወንድ የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል።

የኒውዚላንድ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቡድኑ በልምምድ ላይ ሳለ ድሮን ሲበር እንደነበረ ቅሬታ ማቅረቡን ተከትሎ ነው ፊፋ እና የካናዳ የእግር ኳስ ማኅበር ጉዳዩን መመርመረ የጀመሩት።

ምርመራው መጀመሩን ተከትሎ የካናዳ ኦሊምፒክ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ቤቭ ፕሪስትማን ከኒው ዚላንድ ጋር ከነበራቸው ጨዋታ በፊት ሥራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለቅቀዋል።

የቡድኑ ዋና አስልጣኝ ፕሪስትማን ባወጡት መግለጫ የሥራ ባልደረቦቻቸው ድሮን በማብረራቸው ኃላፊቱን እወስዳለሁ ብለዋል።

የእግር ኳስ ማኅበሩ እና ፊፋ የ38 ዓመቱ አሰልጣኝ ተጋጣሚ ቡድንን በድሮን እንደሰሰለለ መረጃው ነበራቸው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ የካናዳ እግር ኳስ ማኅበር ኃላፊ የሆኑ ሁለት ግለሰቦችንም ለአንድ ዓመት አግዷል።

ፊፋ ተጋጣሚ ቡድኖችን በድሮን መሰለል የእግር ኳስ መርህን የሚጥስ ነው ብሏል።

የካናዳ የእግር ኳስ ማኅበር የገንዘብ ቅጣቱን እና በሦስቱ ግለሰቦች ላይ የተላለፈውን እግድ እንደሚቀበል ገልጾ፤ በቡድኑ ላይ የተጣለው የስድስት ነጥብ ቅጣት ግን ፍትሃዊ አይደለም ብሏል።

ማኅበሩ የነጥብ ቅነሳው ምንም ያላጠፉ የእግር ኳስ ቡድኑ አባላትን መቅጣት ስለሚሆን ውሳኔውን ወደ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ወስዶ እንደሚሞግት አስታውቋል።

ቡድኑ ላይ የተላለፈው ቅጣት ከተሰማ በኋላ አንዳንድ የካናዳ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ቀደም በነበሩ የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ በተመሳሳይ ተጋጣሚ ቡድኖችን ለመሰለል የካናዳ የሴቶች ቡድን ድሮኖች ጥቅም ላይ አውለዋል የሚል ዘገባ እያወጡ ነው።

በቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊ የነበረውን የካናዳ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በፓሪሱ ኦሊምፒክ የመክፈቻ ጨዋታው ኒው ዚላንድን አሸንፏል። ይሁን እንጂ ቡድኑ የተጣለበትን የስድስት ነጥብ ቅጣት ተከትሎ ነጥቡ ከዜሮ በታች -3 ላይ ይገኛል።

ቡድኑ በቀጣይ ከአዘጋጅ አገር ፈረንሳይ እና ከኮሎምቢያ ይገናኛል።