ዩክሬን የኼርሶን መንደሮችን ከሩሲያ ኃይሎች በማስለቀቅ መቆጣጠር ቻለች

የዩክሬን ጦር በደቡብ ኼርሶን የሚገኙ ቁልፍ መንደሮችን ነጻ በማውጣት የሩሲያ ሠራዊት የሚያደርገውን ማፈግፈግ እንዲፋጠን ማድረጉ ተዘገበ።
በዩክሬን የመከላከያ ሚኒስቴር በለጠፈው ቪዲዮ መሠረት 35ኛው ብርጌድ አገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በዳይቪድ ድልድይ ላይ ከፍ አድርጎ ሲያውለበለብ ታይቷል።
ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ በርካታ መንደሮችን በዩክሬን እጅ መግባታቸውን ሪፖርቶች እየጠቆሙ ነው።
የሩሲያ ጦር ከዩክሬን ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ለማፈግፈግ ተገዷል፤ እንዲሁም በደቡብ አቅጣጫም በማፈግፍ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የጦሩ ማፈግፈግ የተሰማው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነት የተፋፋመባቸውን አራት የዩክሬን ግዛቶችን የጠቀለሉበትን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ በተዘጋጁበት ወቅት ነው።
አራቱን ግዛቶች የማጠቃለሉ ድርጊት በዓለም አቀፍ ሕግ ዕውቅና የለውም።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በግዛቶቹ የተከናወኑ ሕዝበ ውሳኔዎችን ቅቡልነት የጎደላቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ማክሰኞ ዕለት ከዜሌንስኪ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሜሪካ ለውሳኔው ዕውቅና እንደማትሰጥ አረጋግጠውላቸዋል።
የሂማስ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ጨምሮ በአሜሪካ የ625 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ዙሪያም መክረዋል።
ሩሲያ አሁንም የኼርሶንን ዋና ከተማ በቁጥጥሯ ስር እንዳደረገች ነው።
ዩክሬናዊያን ዲንፕሮ በሚሉት እና በሰሜን የድናይፐር ወንዝ ያላት ቁጥጥር ፈተና ውስጥ የወደቀ ይመስላል።
ዜሌንስኪ ጦራቸው በደቡብ ዩክሬን “ፈጣን እና ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን” ማድረጉን አስታውቀዋል። በዚህ ሳምንት ብቻ “በደርዘን የሚቆጠሩ መንደሮችን” መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር “የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ በዳቭይዲቭ ብሪድ መንደር በድጋሚ ተውለብልቧል” ብሏል። ነዋሪዎች የዩክሬን ወታደሮች በመንደሯ ሲጓዙ የሚያሳዩ ምስሎችን አስቀርተዋል።
ዜሌንስኪ ማክሰኞ ምሽት በነበራቸው መግለጫ በርካታ በስም የጠቀሷቸው ይዞታዎች ነጻ መውጣታቸውን ተናግረዋል። “ይህም ሁሉንም ነጻ የወጡትን ቦታዎች አያጠቃልልም” ሲሉ አክለዋል።
የዩክሬን ምክትል የአገር ውስጥ ሚኒስትር የቭሄን ኤኒን በበኩላቸው 50 ከተሞች እና መንደሮች ነጻ ወጥተዋል ብለዋል። በኼርሶን 3 ሺህ 500 ዜጎች ነጻ ወጥተዋል ቢሉም በምን ያህል ጊዜ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
የሩሲያ ወታደሮች ሞራል መዳከሙን እና የዩክሬንን ጦር ግስጋሴ ለመግታት ድልድዮችን እያፈረሱ ነው ሲል መከላከያ ሚኒስትሩ አስታውቋል።
በክሬምሊን የተሾሙትና የኼርሶን አስተዳዳሪው ኪርል ስትሬሙሶቭ ነዋሪዎችን “ምንም ዓይነት ጭንቀት ሊገባችሁ አይገባም” ብለዋል።
ከዳቭይዲቭ ብሪድ ሰሜን ምሥራቅ የሚገኙ መንደሮች ነጻ ስለመውጣታቸው ምንም ማረጋገጫ አልተሰጠም። የሩሲያ መከላከያም በአካባቢው ሽንፈት እንደገጠመው አልገለጸም።
የሩሲያ ጦርን በተመለከተ የሚጦምረው ራይባር እንዳለው ጦሩ የመከበብ አደጋ ውስጥ በመግባቱ ለማፈግፈግ ወስኗል።
የኼርሶን የቀድሞው ምክትል አስተዳዳሪ ሮማን ሆሎቭኒያ “መኖሪያ መንደሮች ወድመዋል። ምንም የቀረ ህንጻ የለም” ብለዋል።
ዩክሬን በካርኪቭ እና በዶኔትስከ ድል እየቀናት ነው። ቅዳሜ ዕለት ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያላትን ልይማን በቁጥር ስር አውለዋል። ልይማን በዶኔትስክ ስር ብትሆንም የሉሃንስክ ዋነኛ መዳረሻ መሆኗ ይነገራል።
ኼርሶን፣ ሉሃንስክ እና ዶኔትስክ በሕገወጥ መንገድ በሩሲያ እንዲጠቃለሉ ከተደረጉ ግዛቶች መካከል ናቸው።












