የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጀመራል. . . .ግምቶችን ይዘናል

ታትሟል

የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ዛሬ ምሽት ይጀምራል።

ለአዲሱ የውድድር ዘመን ቢቢሲ ሳምታዊ የውጤት ግምት የሚሰጥ አዲስ ባለሙያ ይዞ መጥቷል- ታዋቂው ክሪስ ሱቶን።

ሱቶን ቀደም ሲል ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ነበር። ቼልሲ፣ አስቶን ቪላ እና ሴልቲክ የተጫወተባቸው ክለቦች ናቸው። በኋላም በአሰልጣኝነት እና በተንታኝነት ሰርቷል።

ለመሆኑ የ2022/23 ውድድር ዘመን የመክፈጫ ጨዋታዎች በምን መልኩ ይጠናቀቃሉ?

ዓርብ

ክሪስታል ፓላስ ከ አርሰናል

አርሰናል ጥሩ የቅድመ ውድድር ዘመን ነበረው። ኮኖር ጋላገር ወደ ቼልሲ ከተመለሰ በኋላ ክሪስታል ፓላስ እንደቀድሞው ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑ ላይ ጥያቄ አለኝ።

ለሚኬል አርቴታ ቡድን ጠንካራ ጨዋታ ይሆናል። ብዙ ነገሮች ግን መድፈኞቹ እንደሚያሸንፉ ይቁማሉ።

ግምት፡ 1- 2

ቅዳሜ

ፉልሃም ከ ሊቨርፑል

እንደ ላውሮ በየሳምንቱ ሊቨርፑል ያሸንፋል እያልኩ መገመት የለብኝም። እንደዚህ አይነት መድሎ ማቆም አለብኝ።

ይህንን ጨዋታ ግን ሊቨርፑል ይሸነፋል ብሎ መገመትም ስህተት ነው።

ሊቨርፑል በኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታ ወቅት ድንቅ ነበር። ቅዳሜ ለፉልሃም ከባድ ጨዋታ ይሆናል። ዓመቱን ሙሉም የሚከብዳቸው ይመስለኛል።

ግምት፡ 0-3

ሊድስ ከ ዎልቭስ

ከፉልሃም እና በርንማውዝ ጋር ሦስተኛው ቡድን ሆኖ የሚወርደው ቡድን ሊድስ ይመስለኛል። ባለፈው ዓመትም ለጥቂት ነው የተረፉት። ካልቪን ፍሊፕስ እና ራፊንሃን የመሰሉ ድንቅ ተጫዋቾቻቸውን ሸጠዋል።

ዎልቭስ ደግሞ ድንቅ ኳስ አቀጣጣይ ተቻዋቾች አሉት። የተጎዳው ራዉል ሂሚኔዝ ባለመኖሩ የአጥቂ ችግር አለባቸው። ስለዚህ የፊት መስመሩን ማን ይመራል?

ይህ ለመገመት ከባድ ጨዋታ ነው።

ግምት፡ 1-1

በርንማውዝ ከ አስቶን ቪላ

በርንማውዝ ያስፈራኛል። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደጉ በኋላ ዝውውሮች ላይ በስፋት አልተሳተፉም።

አስቶን ቪላም በምጠብቀው ልክ ተጫዋቾችን አላስፈረመም። ግን በጣም ብዙ ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾች አሏቸው። በጥሩ ውጤት ለመጀመርም ዕድል ያላቸው ቪላዎች ናቸው።

ግምት፡ 0-1

ኒውካስል ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ፎረስት ከ23 ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ መምጣቱ አስደሳች ነው። ቡድኑ ሮበርትሰንን የመሳሰሉ ጥሩ ተጫዋቾች አሉት። ሄዜ ሊንጋርድ እና ኦሬል ማንጋላን የመሰሉ ድንቅ ተጫዋቾችንም አስፈርመዋል።

ኒውካስል ደግሞ ዘንድሮ መውረድ ስጋት የለበትም። ኤዲ ሃው ድንቅ ሥራ አከናውነዋል።

ዘንድሮም ይህንኑ ያስቀጥላሉ ብዬ አስባለሁ።

ጀምስ ማዲሰንን ከሌስተር ለመግዛት እየሞከሩ ሲሆን ለምን እንደዘገዩ ግልጽ አይደለም።

ይህም ለመገመት የሚከብድ ጨዋታ ይሆናል።

ግምት፡ 1-0

ቶተንሃም ከ ሳውዝሃምፕተን

በቶተንሃም ዙሪያ ብዙ አስደሳች ዜናዎች አሉ። ይህ ግን በየውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የሚፈጠር ነገር ነው።

ሪቻርልሰን በቅጣት በዚህ ጨዋታ ባይሰለፍም እንዴት ከዚህ ቡድን ጋር እንደሚዋሃድ ማየት እፈልጋለሁ።

ዴያን ኩሉስቭስኪ በጥር ወር ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነው። እነዚህን ሁሉ እንዴት አንድ ላይ እንደሚያቀናጁ አላውቅም።

ሳውዝሃምፕተኖች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግምት ሳይሰጣቸው ሜዳ ገብተው ብዙዎችን እያስገረሙ ይወጣሉ።

ከባድ ሽንፈት እና አስደናቂ ድሎችንም አስመዝግበዋል። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር አቻ ተለያይተው የኮንቴው ቶተንሃም አሸንፈዋል።

ይህ ግን የሚደገም አይመስለኝም።

ግምት፡  2-1

ኤቨርተን ከ ቼልሲ

ቼልሲ ለውድድር ዓመቱ የተዘጋጀ አለመመስሉ አስገራሚ ነው። ቡድኑ ገና ተጫዋቾችችን አስፈርሞ አላጠናቀቀም። የተዘጋጀ ቡድንም አይመስለም።

ኤቨርተንም ክፍተቶች አሉበት። ዶምኒክ ካልቨርት-ልዊን በጉዳት ሳሎሞን ሮንዶን እና ሪቻርሊሰን ደግሞ ተዘዋውረዋል። ስለዚህ አጥቂ መስመሩን የሚመራ የለም።

ይህንን ጨዋታ ለማሸነፍ የጉዲሰን ፓርክን ደጋፊ እገዛ ይፈልጋሉ።

ደጋፊው ሊያግዛቸው እንጂ ጎል ሊያስቆጥርላቸው ግን አይችልም።

ግምት፡ 0-2

እሑድ

ሌስተር ከ ብሬንትፎርድ

ያለፈው ዓመት ለሌስተር መጥፎ የውድድር ዘመን አልነበረም። ከሁለት ዓመት የአምስተኛነት ደረጃ የኋሊት ተንሸራተዋል።።

በረኛቸው ካስፐር ሺማይክል ቡድኑን ለቋል። ዌስሊ ፎፋና እና ማዲሰንም ከለቀቁ ለቡድኑ ከባድ ይሆናል።

በሬንትፎርድ ከሳምፕዶሪያ ያስፈረመው አማካዩ ሚኬል ዳምስጋርድ ጥሩ ዝውውር ይመስላል። ከታች ለመጡ ቡድኖች ሁለተኛው የውድድር ዓመት ከባድ ሲሆን ይታያል። የብሬንትፎርድም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል።

ይህ ጨዋታም ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል።

ግምት፡ 1-1

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ብራይተን

ከማንችስተር ዩናይትድ ምን መጠበቅ እንዳለብኝ አላውቅም።

የክርስቲያኖ ሮናልዶ ጉዳይ አለመረጋጋትን ይፈጥራል። አዲሱ አሰልጣን ኤሪክ ቴን ሃግ ያለ አጥቂውም ሊሠሩ ይችላሉ።

በፊት በፊት ኦልድ ትራፎርድ ላይ መጫወት ከባድ ነበር። አሁን አሁን ግን ነገሮች ተለውጠዋል።

አሜክስ ስታዲየም ላይ ባለፈው ዓመት 4 ለ 0 ማሸነፍ ችለዋል። ስለዚህ አይፈሯቸውም። በግራሀም ፖተር የሚመራውን ብራይተን ይመቸኛል። ከዚህ ጨዋታም ነጥብ ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ።

ግምት፡ 1-1

ዌስት ሃም ከ ማንቸስተር ሲቲ

ዌስት ሃም አጥቂውን ጂያንሉካ ስካማካን ከሳምፕዶሪያ አስፈርሟል። ወደ ሙሉ የጨዋታ አቋም የደረሰ ግን አይመስለኝም።

የቡድኑ ችግር የሚመስለኝ የተከላካይ ክፍሉ ነው። በቅርቡ ያስፈረሙት ተከላካዩ ናይፍ አጉዋርድ በጉዳት አይሰለፍም።

ባለፈው ዓመት እንደደረጉት ከሲቲ ጋር አቻ የሚለያዩ አይመስለኝም።

ከሁለት ዓመት በፊት ማንቸስተር ሲቲ በሊጉ መክፈቻ 5 ለ 0 ዌስት ሃምን አሸንፎ ነበር። አሁንም ድሉ የሲቲ ይመስላል።

የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ከሊቨርፑል ጋር ጥሩ አልነበረም። ቡድኑ በዚህ ጨዋታ የሚነቃቃ ሲሆን ኤርሊንግ ሃላንድም የጎል ካዝናውን ይከፍታል የሚል ግምት አለኝ።

ግምት፡ 0-3