ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ የቀጠለው እንቅስቃሴዎችን የተገታው ተቃውሞ በምሥል
በኬንያ ተግባራዊ ሊሆን ታስቦ የነበረውን አዲስ የግብር ሕግን በመቃወም የተጀመረው ተቃውሞ ምንም እንኳን ሕጉ በፕሬዝዳንቱ ውድቅ ቢሆንም እንደቀጠለ ነው።
ተቃዋሚዎች ባለፈው ሳምንት በተካሄዱት ተቃውሞዎች ላይ በፀጥታ ኃይሎች ለተገደሉ ከ30 በላይ ሰዎች ፍትህ ከመጠየቃቸው ባሻገር ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከሥልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ አመጹን ቀጥለውበታል።
ማክሰኞ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. በዋና ከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና የተለያዩ ተቋማት በአብዛኛው ዝግ ሆነው ከተማዋ ጭር ብላ ውላለች።
ተቃዋሚዎቹ በዚህ ሳምንትም ሊቀጥሉት ባቀዱት ተቃውሞ ጎዳናዎችን በመቆጣጠር መንገድ እንደሚዘጉ ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አሳውቀዋል።
የቢቢሲ ዘጋቢዎች እንደተመለከቱት እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጩ ካሉ ምሥሎች መረዳት እንደሚቻለው ዋና ከተማዋን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ተቃውሞ ሲካሄድ ውሏል።
ፖሊሶችም በስፋት ተሰማርተው ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ታይተዋል። ፖሊሶች ተቃወሚዎች ላይ አስላቃሽ ጭስ ሲተኩሱ እና የተወሰኑትን በቁጥጥር ሥር ሲያውኑ እንደነበር ተዘግቧል።
በመዲናዋ ናይሮቢ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች በሰልፈኞች ተዘግተው የነበረ ሲሆን፣ በባሕር ዳርቻዋ ከተማ ሞምባሳ ደግሞ ተሸከርካሪዎች በእሳት ጋይተዋል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ብዙ ያወዛገበውን በምርት እና አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ ግብር የሚጥለውን ሕግ ውድቅ ቢያደርጉም በርካታ ኬንያውያን ቁጣቸውን መንግሥት ላይ መግለጻቸውን ቀጥለዋል።
ባለፉት ሳምንታት በነበረ የታውሞ ስልፍ አብዛኛዎቹ ወጣቶች የሆኑ ኬንያውያን በረቂቅ ደረጃ የነበረው የፋይናንስ ሕግ በፓርላማው ውድቅ እንዲደረግ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ፓርላማው ሕጉን ቢያሳልፈውም ከፍተኛ ተቃውሞውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሕጉን በፊርማቸው እንደማያጸድቁ ከሳምንት በፊት አስታውቀው ነበር።
ይሁን እንጂ የሕጉ ውድቅ መደረግ ሰልፈኞችን አደባባይ ከመውጣት አላገደም።
ሕጉ ውድቅ ይደረግ ሲሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች አሁን ደግሞ “ሩቶ ከሥልጣን ይውረዱ” የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ይገኛሉ።
ከተቃዋሚዎች መካከል አንዳንዶች የንግድ ተቋማት እና ግለሰቦችን ሲዘርፉ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ወጥተዋል።
አንዳንድ ሰልፈኞች ደግሞ ሰላማዊ ሰልፋችን “በዘራፊ ወንበዴዎች ተጠልፎብናል” በሚል “ወንጀለኞችን” ለመያዝ ጥበቃ ሲያደርጉ ታይተዋል።
ለሦስተኛ ሳምንት ማክሰኞ እና ሐሙስ ሲደረጉ በቆዩ የተቃውሞ ሰልፎች ከ39 የማያንሱ ሰዎች መገደላቸውን የመብት ተሟጋቾች እየገለጹ ይገኛሉ።