ቴን ሃግ ቡድናቸው ዩናይትድ ለፉልሃም ጨዋታ ዝግጁ አይደለም ሲሉ ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ በሜዳው ፉልሃምን የሚያስተናግደው ማንቸስተር ዩናይትድ ለጨዋታው ዝግጁ አይደለም ሲሉ አሰልጣኙ ኤሪክ ቴን ሃግ ተናገሩ።

አዲስ ፈራሚዎቹ ማቲያስ ደሊት እና ናሱር ማዝራዊ የቡድኑ ስብስብ ውስጥ ቢሆኑም ቡድኑን የተቀላቀሉት ግን ትናንት ሐሙስ ነው።

ተጫዋቾቹ ከቡድኑ ጋር በበቂ ሁኔታ ባለመዘጋጀታቸው አሰልጣኙ አሰላለፋቸውን በሚመርጡበት ወቅት ጫና እንደሚኖርባቸው ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ተከላካዮቹ ሉክ ሾው እና ሌኒ ዮሮ፤ እንዲሁም አጥቂው ራስመስ ሆይሉንድ በጉዳት ከጨዋታው ውጭ ሆነዋል።

ማዝራዊ እና ደሊትን ለማስፈረም ዩናይትድ ወደ 60 ሚሊዮን ፓውንድ ገደማ ወጪ አድርጓል።

“ቡድኑ ዝግጁ ባይሆንም ሊጉ ይጀምራል” ብለዋል ቴን ሃግ።

ልክ እንደ ዩናይትድ ሁሉ “ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አሰልጣኞች ይኖራሉ ውድድሩን ግድ መጀመር አለብን።”

“ከእውነታው መሸሽ አንችልም። መደበቅም አንችልም። መጋፈጥ ነው ያለብን” ብለዋል ቴን ሃግ።

ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው የኮሚውኒቲ ሺልድ ጨዋታ ተጠበባባቂ ወንበር ላይ የነበረው እና በክረምቱ ዩናይትድን የተቀላቀለው አጥቂው ጆሹዋ ዘርከሲ የመሰለፍ ዕድል ይኖረዋል ተብሏል።

በግራ ተከላካይ ስፍራ ላይ ሉክ ሾው እና ታይለር ማላሲያ በጉዳት ከጨዋታው ውጭ በመሆናቸው ቴን ሃግ ቦታውን በሌላ ተጫዋች የመሸፈን ግዴታ አለባቸው።

ማዝራዊ አንደኛው አማራጭ ሲሆን ዲዮጎ ዳሎ እና ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በኮሙውኒቲ ሽልድ ጨዋታ ወቅት ቦታውን ሸፍነው ተጫውተዋል።

ይህም ሆኖ ግን ለጨዋታው ጠንካራ ቡድን እንደሚያሰልፉ ይጠበቃል።

“ዋናው ነገር የሌሉት ተጫዋቾች አይደሉም” ብለዋል አሰልጣኙ።

“ባለፈው ዓመት ደጋግሜ እንዳልኩት፤ ጉዳዩ መሆን ያለበት መሰለፍ ስለሚችሉ ተጫዋቾች ነው። ጥሩ ስብስብ አለን። ጠንካራ አሰላለፍ ይዘን እንቀርባለን” ብለዋል።

ከጥር ጀምሮ ለዩናይትድ መሰለፍ ያልቻለው ሾው በቅርቡ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ጠቅሰዋል።

“በቅርቡ ይመለሳል። ረዥም ጊዜ አይወስድበትም” ብለዋል ቴን ሃግ።

“ሾው የቡድናችን ቁልፍ ተጫዋች ስለሆነ በፍጥነት እንዲመለስ እንፈልጋለን። በኃይል ግን የሚሆን አይደለም” ብለዋል።