ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩዋንዳ የፖለቲካ ግድያ እንደሚፈጸም ለዩኬ ሚኒስትሮች እንደተነገራቸው ተገለጸ
ስደተኞች ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ እንዲሄዱ የደገፉ የዩናይትድ ኪንግደም ሚኒስትሮች፣ የሩዋንዳ መንግሥት ተቃዋሚዎችን እንደሚያሰቃይና እንደሚገድል በአማካሪዎቻቸው እንደተነገራቸው ተገለጸ።
ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ከመወሰኑ ከሳምንታት በፊት ይህ ማስጠንቀቂያ ለሚኒስትሮቹ እንደተነገራቸውም ተገልጿል።
በአማካሪዎች የተሰነዘረውን ማስጠንቀቂያ በሚሥጥር ለመያዝ የተደረገውን ሙከራ በተመለከተ ምርመራ ተጀምሯል።
ወደ ሩዋንዳ ሊላኩ የነበሩ ስደተኞች እንዲሁም ቢቢሲ፣ ዘ ታይምስ እና ዘ ጋርዲያን የማስጠንቀቂያ መልዕክቱ ይዘት ይፋ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ወደ ሩዋንዳ ሊላኩ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች በረራ ሰኔ ላይ የተሰረዘው የአውሮፓ ኅብረት ሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ጣልቃ በመግባቱ እንደሆነ ይታወሳል።
የለንደን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስደተኞቹን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ውሳኔ ሕጋዊ መሆኑን እንዲፈትሽ የአውሮፓ ኅብረት ሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ ጉዳዮን በቀጣይ ወር ይመለከታል።
ማንነቱ ያልተገለጸ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን ስለ ሩዋንዳ የሰጣቸው 11 ምክረ ሐሳቦች በፍርድ ሂደቱ እንዳይካተቱ የዩኬ መንግሥት ጠይቋል።
እኚህ ባለሥልጣን የአፍሪካን ጉዳዮች በቅርበት እንደሚከታተሉና ስለ ሩዋንዳ ፖሊሲ ዝርዝር ምክረ ሐሳብ እንዲሰጡ እንደተጠየቁ ተገልጿል።
ስለ ሩዋንዳ የሰብዓዊ መብት አያያዝ መረጃ ተጠናክሮ ባለበት ወቅት ነበር ስደተኞቹ ወደ ሩዋንዳ እንዲሄዱ ውሳኔ የተላለፈው።
“የአገሪቱ መንግሥት ሁሉንም እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል። የፖለቲካ ተቃውሞን አይታገስም። ተቃዋሚዎች በዘፈቀደ ይታገታሉ፣ ይንገላታሉ፣ ይገደላሉም” በሚል ስለ ሩዋንዳ መረጃ እንደተሰጠ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ተናግረዋል።
ከቀረበው መረጃ መካከል የተወሰኑት በሚሥጥር እንዲያዙ መደረጉ ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ ካደረጉ መካከል እንደሚጠቀስም ተገልጿል።
“ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት ይህ መረጃ ለመንግሥት እንዲደርስ ተደርጓል። መንግሥት ይህ መረጃ ከተሰጠው በኋላ ለምን ስደተኞቹን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ እንደወሰነ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል” ሲሉ የሕግ ጉዳዮች አዋቂው ጁድ በንቲንግ ተናግረዋል።
ዩኬ ስደተኞችን ወደሌላ አገር ለማዘዋወር ስታስብ ዝርዝር ውስጥ ካስገባቻቸው አገራት መካከል ሩዋንዳ እንድትሰረዝ ተደርጎ እንደነበር ተገልጿል።
ለዩኬ መንግሥት ስለ ሩዋንዳ የደረሱት መረጃዎች ለሕዝብ ይፋ ይደረጉ ወይስ በሚሥጥር ይቀጥሉ በሚለው ላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀጣይ ውሳኔ ያስተላልፋል።
መረጃውን ይፋ ማድረግ የዩኬ የውጭ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለው የተከራከሩ የሕግ አዋቂዎች አሉ።
ሩዋንዳ ስደተኞችን እንድትቀበል 120 ሚሊዮን ፓውንድ መጀመሪያ ላይ ይከፈላትና በቀጣይ ደግሞ ተጨማሪ ክፍያዎች እንደሚፈጸሙ የዩኬ የአገር ውስጥ ሚኒስትር አስታውቋል።
“ሕገ ወጥ የሰው ዝውውርን በመግታት የሰዎችን ሕይወት የሚታደግ ውሳኔ ነው” ሲል የዩኬ መንግሥት ማብራሪያ መስጠቱ ይታወሳል።
ዩኬ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ውሳኔ ካሳለፈች በኋላ 8,000 ስደተኞች ዩኬ ገብተዋል። ዘንድሮ ወደ ዩኬ የገቡ አጠቃላይ ስደተኞች ቁጥር 13,000 ይደርሳል።