አብን የሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ "መዋቅራዊ ጥሰቶች" እና "አንድ ወገን ብቻውን የሚወስንበት እንቅስቃሴ" ታይቷል ሲል ከሰሰ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ "ከተራ የአሠራር ግድፈት" የዘለሉ "ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል" ሲል ከሰሰ። "ገዢው አካል መዋቅራዊ ጥሰቶችን" እንደፈጸመ በማንሳት የከሰሰው አብን፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ "የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅ እና ፍላጎት በአግባቡ ሳይወከል" መታለፉን ገልጿል።

አንድ ወር በሞላው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ካሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው አብን ይህንን ክስ ያቀረበው ቅዳሜ ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። ፓርቲው፣ በምክክር ሂደቱ ታይተዋል ያላቸውን "መዋቅራዊ ግድፈቶች" እና "የመርህ ጥሰቶችን" በጥልቀት መገምገሙን አስታውቋል።

ፓርቲው "በሂደቱ ውስጥ የታየው ሁኔታ ከተራ የአሠራር ግድፈት ወይም ከመደበኛ የፓለቲካ ልዩነት የዘለለ ሆኖ አግኝተነዋል" ሲል በግምገማ የደረሰበትን ድምዳሜ ገልጿል። በሂደቱ ላይ የተፈጸሙት "ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች" የሀገራዊ ምክክሩን "ተዓማኒነት፣ አካታችነት፣ ገለልተኝነት እና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚስገቡ" እንደሆኑም ገልጿል።

አብን ምክክሩ ላይ ለታዩት "መዋቅራዊ ጥሰቶች፣ ጫናዎች እና ወገንተኛ አካሄዶች" ተጠያቂ ያደረገው "ገዢውን አካል" ነው። "መንግሥታዊ መዋቅሮችን የአንድን ቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የማዋል ጥረት እንደሚደረግ በስፋት አስተውለናል" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

"በገዢው አካል" ተፈጽመዋል የተባሉት እነዚህ ድርጊቶች "ሂደቱ የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት" መደቀናቸውንም አስረድቷል።

አብን ይህንን ያለው፣ ወደ ፍጻሜው እየደረሰ ባለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በአጀንዳነት የቀረቡ ስምንት ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ተካርረው በታዩበት ወቅት ነው። በተለይም የአዲስ አበባ ጉዳይ ለምክክር የቀረበበት የፌዴራል ከተሞችን የተመለከተው አጀንዳ በተቃራኒ ወገኖች ከተሰለፉ አካላት የተለያዩ ሀሳቦች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የተመለከቱ አማራጮች በቀረቡበት ወቅት "ጫና ታይቷል" የሚሉ ክሶችም ከታሳታፊዎች ቀርበዋል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ እንደ አገር ግንባታ እና የመንግሥት አደረጃጀት ባሉ "ብዙዎቹ አጀንዳዎች ላይ ጠንከር ያሉ ምክክሮች" የነበሩ ቢሆንም፣ የፌደራል ከተሞች ጉዳይ ላይ "ጠንከር ያሉ አቋሞች" መታየታቸውን አርብ ነሐሴ 8 ቀን ከብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

በምክክሩ ላይ ጫና ስለመኖሩ ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ "በዚህ ሂደት ውስጥ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ምንም አይነት ተጽዕኖ ሳይደረግ ነው እዚህ ደረስነው" ብለዋል። ተጽዕኖ አለመኖሩንም "ስራችንን የፈተሹ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም የውጭ ሰዎችም አይተውታል" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ተቃዋሚው አብንም ትናንት ባወጣው መግለጫው የአዲስ አበባ ጉዳይን በቀዳሚነት አንስቶታል። የአዲስ አበባን "ባለቤትነት" እንዲሁም "ተጓዳኝ የፖለቲካ እና የህግ ማዕቀፎችን" የተመለከተ ምክክር በሚደረግበት ወቅት፣ የከተማዋ ነዋሪዎች "ድምፅና ፍላጎት በአግባቡ ሳይወከል" መቅረቱን ገልጿል።

አዲስ አበባን በተመለከተው ምክክር ላይ "የከተማዋ ሕዝብ እንደ ዋና ባለቤት ሳይቆጠር መታለፉ እጅግ አሳሳቢ ገመና ሆኖ ተመዝግቧል" ብሏል።

"የከተማዋን ነዋሪዎች መብትና ዘላቂ ጥቅም" ወክለው የተገኙ አካላትም "የአንድን ወገን አካል ያልተገራ እና ድንበር የለሽ ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ የከተማውን ህዝብ መብትና ጥቅም አሳልፈው [ሰጥተዋል]" ሲልም ከስሷል።

"የአዲስ አበባ ከተማን መሬት እና አስተዳደር በተናጠል የመቆጣጠር ፍላጎት ታይቷል" ያለው አብን፣ የከተማዋን "ገጽታ ወደ አግላይ ዘውጌያዊነት መለወጥ" የለበትም የሚል አቋም እንዳለው አስታውቋል።

አብን ቅሬታ ያነሳበት ሌላኛው ጉዳይ "የመንግሥት አደረጃጀት እና ቅርፅ" በሚለው አጀንዳ ስር ከቀረቡት አማራጮች ጋር የተያያዘ ነው። አብን በዚህ ጉዳይ ላይ ምክክር በሚደረገበት ወቅት የኢትዮጵያ የመንግሥት ቅርጽ "ፕሬዚዳንታዊ ወይም ከፊል-ፕሬዚዳንታዊ" ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን አማራጭ ማቅረቡን ገልጿል።

ፓርቲው ይህንን አቋም የያዘው "ተወዳዳሪ ዕጩዎች የመላው ሀገሪቱን ዜጎች ድምፅ ለማግኘት ሲሉ ድንበር ተሻጋሪና አስተሳሳሪ የሆኑ ሀገራዊ የፖለቲካ አጀንዳዎችን እንዲያራምዱ ያስገድዳል" በሚል እንደሆነ ጠቅሷል።

ምክክሩ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ግን "የመንግስት አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች" የአገሪቱ መንግሥት ቅርጽ "በፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዚደንት" እንዲኖረው የሚጠይቅ አማራጭ "በድንገት" ማቅረባቸውን አንስቷል።

ይህንን አማራጭ "አምባገነንነትን በሕግ ለማስፈን የሚደረግ ጥረት" ሲል የገለጸው ፓርቲው፣ "በሂደት ስልጣንን በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን እጅ ለማከማቸት እንዲያስችል ህጋዊ ሽፋን ከመስጠት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል" ሲል ተችቷል።

አብን፣ "ሂደቱ ውስጥ የታዩትን አግላይ እና አፋኝ አካሄዶች" በተመለከተ ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በደብዳቤ አቤቱታ ማቅረቡን እንዲሁም ውይይት ማድረጉን ገልጿል። በተመሳሳይም ለገዢው ብልጽግና ደብዳቤ መጻፉን እና ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር መነጋገሩን ጠቅሷል።

ይሁን እንጂ "እስካሁን ድረስ እነዚህን መሠረታዊ ግድፈቶች ለማረም የተወሰደ አዎንታዊ እርምጃ አለመኖሩን" ገልጿል። ወደፊትም "ገዢው አካል የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርገው ስልታዊ ተፅዕኖ እና ጣልቃ ገብነት እየጨመረ እንደሚሄድ አሁናዊ ሁኔታዎች ያመላክታሉ" ሲል ስጋቱን ገልጿል።

"የፓርላማ፣ የህግ አስፈጻሚና የጸጥታ መዋቅሮችን" በመጠቀምም ከምክክሩ "የሚመጡ ምክረ-ሀሳቦችን በተዛባ መልኩ ወደ ራሱ የፖለቲካ መስመር ለማስገባት ሊሞክር ይችላል" ብሏል።

አብን፣ "አንድ ወገን ብቻውን የሚወስንበት፣ አግላይና አምባገነናዊ ስርዓትን የመጫን እንቅስቃሴ የማይቆም ከሆነ" ለሂደቱ "እውቅና የማይሰጥ እና የማይተባበር መሆኑን" በመግለጫው አስታውቋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የለያቸውን ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች የተከፋፈሉት ስምንት ቡድኖች፣ እያንዳንዳቸው በተለያዩ ደረጃዎች ሲያደርጉ የነበሩትን ውይይት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ቡድኖቹ "ያዘጋጇቸው እና የተስማሙባቸው ምክረሃሳቦች" አራት ሺህ አባላት ላሉት ጠቅላላው ጉባኤ ከመቅረቡ በፊት፣ የተናበበ፣ የተጣጣመ እና የተደራጀ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።