ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርሰናል ቪላን አሸንፎ የአምናውን ቁጭት ይወጣል? ዩናይትድስ የብራይተን ጫናን ይቋቋማል?
አምና በውድድሩ ማብቂያ ላይ አርሰናል በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በቪላ ባይሸነፍ ኖሮ የ20 ዓመታት የዋንጫ ፍላጎቱ ምላሽ ያገኝ ነበር።
ይህ ብቻ አይደለም አምና አርሰናል በደርሶ መልስ ጨዋታ የተሸነፈው በቪላ ነበር።
የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን “ይህን ጨዋታ እስክመለከት ድረስ በጉጉት ነው የምጠብቀው” ይላል።
ዩናይትድም ቢሆን ቀደም ባለው ዓመት የውድድር ዘመን መጀመሪያ ላይ ወደ ብራይተን ባቀኑ ወቅት የደረሰበት ከባድ ሽንፈት የሚታወስ ነው።
ክሪስ ሱተን የ2024/25 የውድድር ዓመት የሁለተኛ ሳምንት የጨዋታ ግምቶችን እንደሚከተለው ሰጥቷል።
ቅዳሜ
ብራይተን ከ ዩናይትድ
ባለፈው ሳምንት ጨዋታ ብራይተን ኤቨርተንን በቀላሉ ማሸነፍ ችሏል። በጨዋታው ኪሮ ሚቶማ እና አዲሱ ፈራሚ ሚንቴ ምርጥ ነበሩ።
ብራይተን በአዲሱ አሠልጣኛቸው ስር ሆነው በመጀመሪያ ጨዋታ ድል ማድረጋቸው ጥሩ ጅማሬ ነው።
ዩናይትድም ቢሆን አሳማኝ ባይሆንም የውድድር ዘመኑን በድል ጀምሯል። በዚህ ጨዋታ ነጥብ የሚጋሩ ይመስለኛል።
ግምት፡ ብራይተን 1 - 1 ዩናይትድ
ክርስታል ፓላስ ከ ዌስት ሃም
ክርስታል ፓላስ ከ ብሬንትፎርድ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ጥሩ ቢጫወቱም እንደ አለመታደል ሆኖ ተሸንፈዋል።
በዌሰት ሃም ደግሞ አዲስ መነቃቃት ተፈጥሯል።
ይህ ጨዋታ ግን በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ ፓላስ 2 - 2 ዌስት ሃም
ፉልሃም ከ ሌስተር
ፉልሃም ከዩናይትድ በነበረው ግጥሚያ ጥሩ ቢጫወታም ከመሸነፍ ግን አላመለጠም። እርግጠኛ ነኝ ከዚያ ጨዋታ ነጥብ ይዘው መውጣት እንደሚገባቸው ያስባሉ።
ሌስተር በአንጻሩ በባለፈው ጨዋታቸው በቶተነሃም ተበልጠው ቢታዩም በሁለተኛው አጋማሽ ጎል አስቆጥረው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።
ጄሚ ቫርዲን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ተመልሶ ጎል ሲያስቆጥር መመልከት ያስደስታል።
ይህን ጨዋታ ባለሜዳው ፉልሃም የሚያሸንፍ ይመስለኛል።
ግምት፡ ፉልሃም 2 - 0 ሌስተር
ማንቸስተር ሲቲ ከ ኢፕስዊች
ኢፕስዊች እንደ አርማንዶ ብሮሃ፣ ሳሚ ሳዝሞዲች፣ ሊያም ዴልፍ እና ኦማሪ ሃቺሰን ያሉ ምርጥ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።
ከዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው ኢፕስዊች በሊጉ እንደሚቆይ ተስፋ አድርጋለሁ።
ይህን ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ጨዋታ ቢያስ እስከ 60ኛው ደቂቃ አስመስክሯል።
አሁን ግን የሚጫወተው ከሻምፒዮኑ ሲቲ ጋር በመሆኑ በሰፊ የግብ ልዩነት እንደሚሸነፍ እገምታለሁ።
ግምት፡ ሲቲ 4 - 0 ኢፕስዊች
ሳውዝሃምፕተን ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ሳውዝሃምፕተን ከኒውካስል በነበረው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበሩ። የኒውካስል ተከላካይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላ እንኳ ጎል ማስቆጠር ተስኗቸው ነበር።
ሳውዝሃምፕተን ከዚያ ጨዋታ የሆነ ነገር ማግኘት ነበረበት።
ፎረስት በበኩሉ ዳኒሎን አስቀያሚ በሆነ ጉዳት ማጣቱ ለቡድኑ ከባድ አደጋን ይዞ የሚመጣ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህን ጨዋታ ፎረስት ያሸንፋል ብዬ እገመታለሁ።
ግምት፡ ሳውዝሃምፕተን 0 - 1 ፎረስት
ቶተነሃም ከ ኤቨርተን
ቶተነሃም ከሌስተር በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቢያንስ 8 ግብ የሚያስቆጥርበትን ዕድል አግኝቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ዕድሎቹን መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። በዚያ ጨዋታ አቻ ቢለያይም እኔ ግን የሰሜን ለንደኑ ክለብ እንደተሸነፈ ነው የምቆጥረው።
ኤቨርተን እንዲሁ ደካማ አቋም አሳይቶ በብራይተን ተሸንፏል። ቶተነሃም ይህን ጨዋታ በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸንፋል የሚል ግምት አለኝ።
ግምት፡ ቶተነሃም 3 - 0 ኤቨርተን
አሰቶን ቪላ ከ አርሰናል
አርሰናል ባለፈው ሳምንት ከዎልቭስ ጋር የነበረውን ጨዋታ ተቆጣጥሮ በመያዝ አሸንፏል።
ቪላ ደግሞ ከሜዳው ውጪ ዌስት ሃምን አሸንፎ መድፈኞቹን በሜዳቸው ለማስተናገድ ተሰናድቷል።
ይህ ጨዋታ አቻ የሚጠናቀቅ ቢመስለኝም አርሰናል በጠባብ ውጤት ሊያሸንፍ የሚችልበት ዕድል አለ።
ግምት፡ ቪላ 1 - 2 አርሰናል
ዎልቭስ ከ ቼልሲ
በርካታ ተጫዋቾች ያሏቸው የቼልሲው አሠልጣኝ ለዚህ ጨዋታ የሚመርጧቸውን ተጫዋቾች ለመመልከት ጓጉቻለሁ።
ዎልቭስ በሜዳቸው እንደመጫወታቸው ከቼልሲ ጋር ነጥብ ለመጋራት ያቅታቸዋል ብዬ አላስብም።
ግምት፡ ዎልቭስ 1 - 1 ቼልሲ
ሊቨርፑል ከ ብሬንትፎርድ
ብሬንትፎርድ ሁለት ጎሎችን አስቆሮ ፓላስን ማሸነፋቸው ዕድለኛ ያደርጋቸዋል። ወሳኝ የሆነው አጥቂያቸው አይቫን ቶኒ ወደ ልምምድ ተመልሷል። ይሁን እንጂ ቶኒ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናል የሚል ጨምጨምታ አለ።
ሊቨርፑል በመጀመሪያ ጨዋታው በጣም ምርጥ ነበር። በዚያ ጨዋታ ሞ ሳላህ ንቁ ነበረ። ብሬንትፎርድ የሊቨርፑል የአጥቂ መስመር መቋቋም የሚችል አይመስለኝም።
ግምት፡ ሊቨርፑል 3 - 1 ብሬንትፎርድ