የፌደራሉ መንግሥት የአድዋ ከተማን መያዙ ተገለጸ

ታትሟል

የፌደራል መንግሥቱ ጥምር ጦር ታሪካዊቷን አድዋ ከተማ ከትግራይ ኃይሎች ማስለቀቁ ተዘገበ።

አሶሺዬትድ ፕሬስ የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኛን ጠቅሶ እንደዘገበው የትግራይ ኃይሎች “ከፍተኛ ሽንፈት” ካጋጠማቸው በኋላ ጥምር ጦሩ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 12/2015 ዓ.ም. አድዋን ይዟል።

አሶሺዬትድ ፕሬስ ዋቢ ያደረገው የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኛ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የምትገኘው አድዋ በቁጥጥር ሥር የዋለችው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሠራዊት ጥምር ጦር ነው ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት “ቁልፍ” የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን መቆጣጠሩን ቀጥሏል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ይሁን እንጂ መግለጫው የትኞቹን ከተሞች እንደተቆጣጠረ በዝርዝር ያለው ነገር የለም።

መከላከያ ከተሞቹን ሲቆጣጠር “በከተሞች ውጊያ ሳይደረግ የህወሓትን ወታደራዊ አቅም ለማሽመድመድ የሚያስችል ስልት ተጠቅሟል” ሲል መግለጫው አክሏል።

ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አርብ ዕለት በአድዋ ላይ በተፈጸመ የአየር ድብደባ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ነዋሪዎች መሞታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የረድዔት ድርጅት ሰራተኛን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማክሰኞ ጥቅምት 8/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረምን መያዙን አስታውቋል።

መንግሥት ኮረም ከተማን ይዣለሁ ይበል እንጂ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት ለቢቢሲ በሰጡት ቃል፣ ኮረም አሁንም በኛ ቁጥጥር ሥር ናት ብለው ነበር።

ፕሮፌሰር ክንደያ፣ ረቡዕ ምሽት ጥቅምት 9፣2015 ዓ.ም ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ‘ኮረምን ይዘው ያሉት የኛ ኃይሎች ናቸው’ ካሉ በኋላ፣ ከኮረም አቅራቢያ በበርካታ አካባቢዎች ብርቱ ውጊያ እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

የፌደራሉ መንግሥት ጥምር ጦር ሽረ፣ አላማጣ እና አድዋ ከተሞች በተጨማሪ አክሱም ከተማን ስለመያዙ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች በስፋት እየወጡ ይገኛሉ። 

ለአምስት ወራት የቆየው የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ጦርነቱ ካገረሸበት ነሐሴ ወር ጀምሮ በትግራይ ላይ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የረድዔት ሰራተኞች ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በቅርቡ በትግራይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ባልለየ መልኩ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ብሏል።

“ሰላማዊ ነዋሪዎችን ባልለየ መልኩ በመኖሪያ አካባቢዎች ጨምሮ እየደረሰ ባለው ጥቃት ንጹሃን ዜጎች እየተገደሉ ነው። መሰረተ ልማቶች እየወደሙ ነው። እንዲሁም መሰረታዊ አገልግሎቶች እየተገደቡ ነው" በማለት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናግረዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር በበኩላቸው "በሽረ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት የፈጸሙት ሰላማዊ ሰዎችን ያልለየ ጥቃት አሳሳቢ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።

በቅርቡም የአሜሪካ መንግሥት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለድርድር መምጣታቸውን ድጋፍ እንደሚሰጥ በጠቀሰበት መግለጫም፣ጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ የዘፈቀደ ድብደባ መፈጸሙ እንዳሳሰበው ገልጿል።

የሰብዓዊ እርዳታ መጀመር

የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ባስለቀቃቸው ከተሞች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራ እንደሚጀመር ሲገልጽ ቆይቷል።

ዛሬም በወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብአዊ የእርዳታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እየሠራ ይገኛል ብሏል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ፣በሽረ አየር ማረፊያ በኩል እንዲሁም በሌሎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በገቡ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን እና ከሚመለከታቸው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ድርጅቶች ጋር እንደሚጣመር አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ መስመሮችን ለማስፋፋት ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።

“የሰሜን ጎንደር-ሽረ እንዲሁም የኮምቦልቻ-ደሴ-ቆቦ-አላማጣ መስመሮች ለመክፈት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው” ብሏል በዛሬው መግለጫ።