አርጀንቲና፣ ቺሊ፣ ኡራጓይና ፓራጓይ የዓለም ዋንጫን በጥምረት ለማዘጋጀት ጠየቁ

 የዓለም ዋንጫ

የፎቶው ባለመብት, JEWEL SAMAD

ታትሟል

አርጀንቲና፣ ቺሊ፣ ኡራጓይ እና ፓራጓይ በአውሮፓውያኑ 2030 ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫን በጋራ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቀረቡ።

የአለም ዋንጫ የመጀመሪያውን ውድድር በአውሮፓውያኑ 1930 ያስተናገደችው ኡራጓይ የአለም ዋንጫ መቶኛ አመቱን ሲያከብር ወደተጀመረባት አገር ማምጣት እንደምትፈልግ አስታውቃለች።

የደቡብ አሜሪካዎቹ አገራት የአለም ዋንጫን በጋራ ለማዘጋጅት መጠየቃቸውንም አስመልክቶ “ ይህ የአንድ አህጉር ህልም ነው” በማለት የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ኮንሜቦል) ፕሬዝዳንት አሌሃንድሮ ዶሚኒጌዝ ተናግረዋል።

ከደቡብ አሜሪካዎቹ አገራት በተጨማሪ የአውሮፓ ሃገራቱ ስፔን እና ፖርቹጋል በጋራ ለማዘጋጀት ውድድሩ ላይ ቀርበዋል።

ሞንቴቪዲዮ ሴንቴናሪዮ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያው የአለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ኡራጓይ አርጀንቲናን ያሸነፈች ሲሆን ፕሬዚዳንት አሌሃንድሮ ዶሚኒጌዝ በዚህ ስታዲየም ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

“ተጨማሪ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ይኖራሉ ፣ ነገር ግን የዓለም ዋንጫ ጨዋታ 100 አመቱን የሚያከብረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው ስለዚህ ወደተጀመረበት ወደ ቤቱ መምጣት አለበት” ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ቺሊ የዓለም ዋንጫን በአውሮፖውያኑ 1962 ስታስተናግድ፣ አርጀንቲና ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1978 አዘጋጅታለች።

"የአለም ዋንጫ ውድድር ከ100 አመት በኋላ በተጀመረበት ቦታ መካሄዱ ትክክለኛ ነው" በማለት የኡራጓይ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ኢግናሲዮ አሎንሶ ተናግረዋል።

የ2022 የአለም ዋንጫ በኳታር የሚካሄድ ሲሆን ካናዳ፣ሜክሲኮ እና አሜሪካ የ2026 የጋራ አስተናጋጅ ይሆናሉ።

ፊፋ የ2030 አስተናጋጅን ከሁለት አመት በኋላ፣ በ2024 ለመምረጥ እቅድ ይዟል።

የዩናይትድ ኪንግደም እና የአየርላንድ ሪፐብሊክ የእግር ኳስ ማህበራት ለ2030ው የአለም ዋንጫ አስተናጋጅነት ላለመወዳደር እና በምትኩ ዩሮ 2028ን በጋራ ለማዘጋጀት በሚደረገው ጥረት ላይ ለማተኮር ተስማምተዋል።