ቢዮንሴ ታሪክ የሠራችበት የግራሚ ሽልማት ተከናወነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
32ኛ የግራሚ ሽልማቷን ማሳካት የቻለችው ቢዮንሴ በርካታ ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ለመሆን በቃች።
ዘፋኟ ሬይኔሰንስ በተሰኘው አልበሟ በምርጥ የዳንስ/ኤሌክትሮኒክ አልበም ዘርፍ በማሸነፍ ነው አዲስ ታሪክ የጻፈችው።
በዚህም 31 ሽልማቶችን በማንሳት ለ20 ዓመታት ያህል በቡልጋሪያዊ-እንግሊዛዊው የሙዚቃ ቀማሪ ጆርጅ ሶልቲ ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን አሻሽላለች።
“ስሜታዊ ላለመሆን እየጣርኩ ነው” ያለችው አርቲስቷ “ዛሬ ሽልማቴን ብቻ እየተቀበልኩ ነው” ስትል አክላለች።
ታዋቂ ከመሆኗ በፊት የመድረክ ልብሶቿን የሚያዘጋጅላትንና በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈውን አጎቷን ጆኒን ጨምሮ ቤተሰቦቿን አመስግናለች።
ግራሚ በሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ትልቁ ሽልማት እንደሆነ ይገለጻል።
የእሑዱ ዝግጅት ላይ አዴል፣ ሃሪ ስታይልስ፣ ቴይለር ስዊፍት፣ ሊዞ፣ ሻኒያ ትዋይን እና ስቲቪ ዎንደር ተገኝተው ምሽቱን አድምቀውታል።
አዴል 'ኢዚ ኦን ሚ' በተሰኘው ሥራዋ በምርጥ የፖፕ አቀራረብ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች። ሽልማቱን ለልጇ አንጄሎ መታሰቢያ እንዲሆንላት አበርክታለች።
“የዘፈኑን የመጀመሪያ አዝማች መታጠቢያ ቤት ሆና ስለልጇ ሕይወት ስታስብ እንዳጻፈችው አንስታለች።
'ጀስት ላይክ ዛት' በሚለው ዘፈኗ ቦኒ ራይት የዓመቱ ምርጥ ዘፈን ሽልማትን አሳክታለች። በዚህ ዘርፍ ቴይለር ስዊፍት እና ቢዮንሴ ታጭተው ነበር።
ራይት በዘፈኗ በልጇ ሞት የተጎዳች እናት የልጇን ልብ በንቅለ ተከላ ካገኘ ሰው መጽናናትን ስታገኝ የሚገልጽ ታሪክ አንስታለች።
ሽልማቷን ከተቀበለች በኋላ የ72 ዓመቷ ዘፋኝ “ለዚህ ዘፈን ዕውቅና በመስጠታችሁ ክብር ተሰምቶኛል” ብላለች።
በሎስ አንጀለስ የተከናነውን ሥነ ሥርዓት ባድ በኒ በደማቅ ሁኔታ ከፍቶታል።
የሽልማት ስነ ስርዓቱ በተለያዩ ዘፋኞች ደምቆ አምሽቷል።
የሂፕ-ሆፕን 50ኛ ዓመት በማስመልከት ደግሞ ሁለት ደርዘን የሚሆኑ አርቲስቶች መድረኩ ላይ ተንፈላሰውበታል።
ቢዯንሴ በድምሩ አራት ሽልማቶችን ብታገኝም የመጀመርያዎቹ ላይ ለመድረክ ሳትበቃ ቀርታለች። ይህም የሆነው በሎን አንጀለስ ትራፊክ መጨናነቅ በጊዜ መድረስ ባለመቻሏ ነበር።
የመድረኩ አጋፋሪ ትሬቨር ኖዋ "ቢዮንሴ ትራፊክ መጨናነቅ የሚያቆማት አይመስለኝም ነበር፤ ከጊዜና ከቦታም በላይ ትመስለኝ ነበር" ሲል ቀልዷል።












