ጃፓን በዱር ዝንጀሮዎች ላይ እርምጃ ልትወስድ ነው

ታትሟል

ነዋሪዎችን እያሸበሩ ያሉ የዱር ዝንጀሮዎችን ለመቆጣጠር የጃፓን ፖሊሶች መድኃኒት ያላቸው ጥይቶች ለመጠቀም ወስነዋል።

ባለፉት ሳምንታት በያማጉቺ ከተማ ሕጻናትና አዛውንቶችን ጨምሮ 42 ሰዎች በዝንጀሮዎቹ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ለጥቃቶቹ በጃፓን የሚገኝ አንድ የዝንጀሮ ዝርያ ተጠያቂ ሆኗል።

እነዚህ ዝንጀሮዎች በመላው አገሪቱ ቢገኙም እንደነዚህ ያሉ ጥቃቶች ያልተለመዱ ናቸው።

"በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ጥቃት ማየት አልተለመደም" ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የከተማው ባለሥልጣን ገልጸዋል።

"መጀመሪያ ላይ ሕጻናት እና ሴቶች ብቻ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አዛውንቶች እና አዋቂ ወንዶችም ጥቃት እየደረሰባቸው ነው" ብለዋል።  

እንስሳቱን በወጥመዶች ለመያዝ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ከተፈጸመው የመጀመርያው ጥቃት ጀምሮ ፖሊስ ችግሩን ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ ፍሬ አላፈራም።

ባለሥልጣናት ጥቃቶቹ በአንድ ወይም በብዙ ዝንጀሮዎች ስለመፈጸማቸው እርግጠኛ አይደሉም።

የአራት ዓመት ሴት ልጅ የምትኖርበት ቤት ተሰብሮ የተቧጨረች ሲሆን በሌላ አጋጣሚ ድግሞ አንድ ዝንጀሮ መዋዕለ ሕጻናት ክፍል ውስጥ ተገኝታለች።

አንዳንድ ነዋሪዎች በቤታቸው ውስጥ ብዙ ዝንጀሮዎች እንደገቡ ሪፖርት አድርገዋል።ተንሸራታች መስኮቶችን ከፍተው ወይንም የተከፈተ በር ተጠቅመው መግባታቸው ታውቋል።

አንድ አባት ለጃፓን ፕሬስ "ታችኛው ክፍል ውስጥ የማልቅስ ድምጽ ሰምቼ ስለነበር በፍጥነት ወረድኩ። ስደርስ ዝንጀሮ ልጄ ላይ ሆኖ አየሁ" ብለዋል።

የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲባሉ የነበሩት እነዚህ የጃፓን የዝንጀሮ ዝርያዎች ቁጥር አሁን ጨምሯል።

አሁን በዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ማኅበር የመጥፋታቸውን ስጋት "አነስተኛ" በሚለው ደረጃ ውስጥ መድቧቸዋል።

የቁጥራቸው መጨመር “በሰዎች እና በዝንጀሮዎች መካከል ከባድ ግጭቶችን አስከትሏል” ሲል በያማጋታ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ያሳያል።

ለዚህ ደግሞ በሰዎች እና በዝንጀሮዎች መካከል ያለው መቀራረብ መቀነስ ነው ሲል በጥናቱ ጠቁሟል።

በዝንጀሮዎች ዙሪያ ያለው አመለካከት መቀየር፣ የሰዎች ባህሪ ለውጥ እና የደን አካባቢዎች ለውጦችም እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል።