ዩክሬን ዘሌንስኪን ለመግደል በማሴር የተጠረጠረችን ሴት በቁጥጥር ሥር አዋለች

ታትሟል

ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪን ለመግደል ከሩሲያ ሴራ ጋር በተያያዘ አንዲት ሴትን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

መሥሪያ ቤቱ እንዳለው ግለሰቧ ፕሬዚደንቱ ሰኔ ወር ላይ በጎርፍ የተመታችውን ማይኮላይቭን ከመጎብኘታቸው ቀደም ብሎ የጉዟቸውን መርሃ ግብር ለማወቅ ሞክራለች።

ዩክሬን ብዙ ጊዜ የሞስኮን ጦር ለመርዳት መረጃ ያስተላልፋሉ በሚል ሩሲያን የሚደግፉ ነዋሪዎችን ትከሳለች።

ፕሬዚደንት ዘሌንስኪ ስለእስሩ መስማታቸውን አረጋግጠው፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ስለነበረው ሁኔታ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።

ሩሲያ ግን እስካሁን እስሩን በተመለከተ የሰጠችው አስተያያት የለም።

የዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤት (ኤስቢዩ) ባወጣው መግለጫ ግለሰቧ ለሩሲያ የደኅንነት መረጃ ለማስተላለፍ ስትሞክር እጅ ከፍንጅ መያዟን ገልጿል።

ግለሰቧ ከጉብኝቱ ቀደም ብሎ ዘሌንስኪ በደቡባዊቷ ማይኮላይቭ ግዛት ያላቸውን እቅድ ለማወቅ የደኅንነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ ሞክራለች ሲልም ከሷል።

በተጨማሪም ኩሽና ውስጥ ተጠርጣሪዋ ጭንብል ካጠለቁ የጸጥታ መኮንኖች ጋር ሆና የሚያሳይና ፊታቸው እንዲደበዝዝ የተደረገ ምስል አጋርቷል።

ዘሌንስኪ ሰኔ ወር ውስጥ ከካኾቭካ ግድብ መፍረስ ጋር ተያይዞ የደረሰውን ጉዳት ለማየት እንዲሁም ሐምሌ ወር ላይ በሩሲያ ከተፈፀመው ድብደባ በኋላ ማይኮላይቭን ጎብኝተዋል።

የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ከፕሬዚደንቱ ጉዞ በፊት ሴራውን ማወቁንና ተጨማሪ የደኅንነት እርምጃዎች መውሰዱን ገልጿል።

መሥሪያ ቤቱ ሩሲያ በማይኮላይቭ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ድብደባ ለመፈፀም አቅዳ ነበር የሚል ክስ የሰነዘረ ሲሆን፣ ግለሰቧም በሩሲያ ጦር ኢላማ ሊሆኑ የሚችሉ የኤሌክትሮኒክ ጦር ሥርዓት እና የጥይት መጋዘኖች መገኛ ቦታዎችን መረጃ ለመስጠት እየሞከረች እንደነበር ጨምሮ ገልጿል።

እንደ ኤስቢዩ ከሆነ ግለሰቧ ፕሬዚደንት ዘሌንስኪ ሐምሌ ወር ላይ በጎበኟት ኦቻኪቭ በሚባል ከተማ ውስጥ ትኖር የነበረ ሲሆን እዚያ ባለ የጦር ሰፈር በሚገኝ ሱቅ ውስጥ ትሰራ ነበር።

የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ በጉብኝቱ ወቅት በዩክሬን ፕሬዚደንት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለመከላከል ተጠርጣሪዋን አለማሰሩንና እርምጃ አለመውሰዱም ታውቋል።

ሆኖም ከጉብኝቱ በኋላ ስለግለሰቧ ድርጊትና ከሩሲያ ስለተቀበለችው የቤት ሥራ ለማወቅ የደኅንነት ሰዎች ሲከታተሏት እንደነበር ኤስቢዩ ጨምሮ ገልጿል።

ግለሰቧ ወደ አካባቢው በማምራት የዩክሬንን የጦር መሠረተ ልማቶች ምስል በማንሳት እና ቪዲዮዎችን ቀርጻለች ሲል መግለጫው ከሷል።

ያለ ፈቃድ የጦር መሣሪያዎችን እና የወታደሮችን እንቅስቃሴ የተመለከቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ክስ ይቀርብባታልም ተብሏል።

ግለሰቧ በዚህ ክስ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች 12 ዓመታትን በእስር ልታሳልፍ ትችላለች።

የዩክሬን የጸጥታ ኃይሎች ለሩሲያ የአየር ጥቃት ኢላማዎችን በማመላከት ረድተዋል ያሏቸውን በርካታ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።