የሃንጋሪ የሚትዎሮሎጂ አገልግሎት ኃላፊዎች በተሳሳተ ትንበያ ምክንያት ከሥራ ተባረሩ

ታትሟል

በሃንጋሪ የተሳሳተ የአየር ትንበያ ቁጣ ማስነሳቱን ተከትሎ ሁለት የአገሪቱ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሥራ ተባረሩ።

የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀንን ለማክበር “የአውሮፓ ትልቁ የርችት ትዕይንት” ተብሎ የሚጠራውን ብሔራዊ ክብረ በዓል ለማክበር ቅዳሜ ምሽት ከፍተኛ ዝግጅት ተሰናድቶ ነበር።

ነገር ግን  መርሃ ግብሩ ሊጀመር ከሰባት ሰዓት በፊት የከፋ የአየር ሁኔታ ያጋጥማል በሚል ዝግጅቱ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

ሆኖም እንደተተነበየው ሳይሆን የአየር ሁኔታው ምቹ እና የተስማማም ሆኖም በመገኘቱ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ኃላፊ እና ምክትል ኃላፊው ከሥራ  ተባረዋል።

በመካከለኛው ቡዳፔስት በሚገኘው የዳኒዩብ ወንዝ አምስት ኪሎሜትር የሚሸፍን 40 ሺህ ርችቶች ተዘጋጅተው ነበር፤ ይህም አብዛኛውን ጊዜ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ይመለከቱታል።

መንግሥት በደረሰው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ትንበያ  ምክንያት ዝግጅቱን ለአንድ ሳምንት አራዝሞታል።

ነገር ግን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት እንደተነበየው አውሎ ንፋስ የተቀላቀለበት ዝናብ አቅጣጫውን ቀይሮ በምትኩ የምሥራቅ ሃንጋሪን አንዳንድ ክፍሎች የመታ ሲሆን በዋና ከተማዋ ላይ ምንም ሳይፈጠር ቀርቷል።

ተቋሙ እሁድ ዕለት ለተፈጠረው ስህተት በይፋዊ ፌስቡክ ገጹ ላይ ይቅርታ ጠይቋል። በፌስቡክ ላይ በሰፈረው ጽሁፍ “አይፈጠርም ተብሎ የታሰበው ነገር መከሰቱን እና እርግጠኛ አለመሆን የአየር ትንበያ አካል ነው” ሲል ገልጿል።

ሆኖም ይቅርታው የታሰበውን ውጤት አላመጣም።

ሰኞ ዕለት የአገሪቱ የኢኖቬሽን ሚኒስትር ላስዝሎ ፓልኮቪች የሚትሮዎሎጂ አገልግሎት ኃላፊዎችን አሰናብተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በሃንጋሪያውያን መካከል ያለውም ምላሽ የተቀላቀለ ሆኗል።

ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በአጎራባች ዩክሬን ባለው ጦርነት ምክንያትና እንዲሁም ከተከሰተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ጋር ተያይዞ የርችት ዝግጅቱ እንዲሰረዝ በመጠየቅ ፊርማቸውን አኑረዋል።

የመንግሥት ደጋፊዎች በበኩላቸው በተቋሙ ኃላፊዎች ቁጣቸውን በመግለጽ ትርኢቱ አሁን እንደታቀደው በሚቀጥለው ቅዳሜ እንደሚከናወን ተስፋ አድርገዋል።