የሕንድ እና የቻይና ወታደሮች በአወዛጋቢ የድንበር አካባቢ መጋጨታቸው ተገለጸ

ታትሟል

ከአንድ ዓመት በላይ ተረጋግቶ በቆየው በአወዛጋቢው የድንበር አካባቢ ሠራዊቷ ከቻይና ወታደሮች ጋር መጋጨቱን ሕንድ አስታወቀች።

አገራቱ ከሁለት ዓመት በፊት በድንበር አካባቢ ባጋጠመው ግጭት ሳቢያ ቢያንስ 24 ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ሲጥሩ ቆይተዋል።

ነገር ግን የሕንድ ጦር ሠራዊት ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል አሩናቻል ፕራዴሽ ውስጥ ባለፈው አርብ ግጭት ማጋጠሙን አመልክቷል።

ተከሰተ በተባለው ግጭት ዙሪያ ቻይና እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

በግጭቱ ከሁለቱም ወገኖች ጥቂት ወታደሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ቀላል ጉዳት መድረሱም ተነግሯል። ሮይተርስ የሕንድ ወታደራዊ ምንጭን ጠቅሶ ስድስት ሕንዳውያን ወታደሮች መቁሰላቸውን ዘግቧል።

የሕንድ ጦር ሠራዊት ግጭቱን ተከትሎ “ሁለቱም አገራት ወታደሮቻቸውን ወዲያውኑ ከአካባቢው አስወጥተዋል” በማለት፣ የሁለቱም አገራት ጦር አዛዦች ተገናኝተው “ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን” መወያየታቸው ተነግሯል።

የሕንድ የመከላከያ ሚኒስትር ራጅናት ሲንግ ዛሬ ማክሰኞ ለአገሪቱ ፓርላማ እንደተናገሩት፣ ከወታደሮቻቸው መካከል “የተጎዳ ወይም ክፉኛ የቆሰለ የለም” በማለት፣ ጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንደተያዘ አመልክተዋል።

ጨምረውም “የሕንድ ሠራዊት አዛዦች ወዲያውኑ ጣልቃ በመግባታቸው፣ የቻይና ወታደሮች ወደ ይዞታቸው እንዲመለሱ አድርገዋል።”

ሕንድ እና ቻይና በአግባቡ ያልተካለለ 3,440 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን አወዛጋቢ ድንበርን የሚጋሩ አገራት ናቸው።

በድንበር አካባቢ ያሉ ወንዞችን፣ ሐይቆችን እና በረዷማ ተራሮችን ተከትሎ በዓለም ግዙፍ ሠራዊት ያላቸው የሁለቱ አገራት ወታደሮች በተደጋጋሚ ለፍጥጫ እና ለግጭት ተዳርገዋል።

ከ45 ዓመታት በኋላ የሰው ነፍስ የጠፋበት ነው በተባለው እና በአውሮፓውያኑ 2020 በተከሰተው የድንበር ላይ ግጭት ከሕንድ 20 ከቻይና በኩል ደግሞ ቢያንስ አራት ወታደሮች ተገድለዋል። ይህንንም ተከትሎ አገራቱ ውጥረቱን ለማርገብ ሲሞክሩ ቆይተዋል።

በጥር ወር 2021 (እአአ) ደግሞ በተከሰተ ሌላ ግጭት ከሁለቱም ወገን ያሉ ወታደሮች ላይ የመቁሰል ጉዳት ደርሶ ነበር።

ባለፈው መስከረም ወር ሕንድ እና ቻይና ከምዕራባዊ የሂማሊያ ተራራ ጋር ከሚወሰነው አወዛጋቢ የድንበር አካባቢ ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት ተስማምተው ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።