ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራቅ የሺዓ መሪው ራሳቸውን ከፖለቲካ ማግለላቸውን ተከትሎ በተነሳ ብጥብጥ 15 ሰዎች ተገደሉ
በኢራቅ የሺዓ መሪው ሙክታዳ አል ሳድር ከፖለቲካ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ በተነሳ ግርግር አስራ አምስት ሰዎች ተገደሉ።
በኢራቋ መዲና ባግዳድ የተነሳው ሁከት በጸጥታ ኃይሎችና በፖለቲከኛው ደጋፊዎች መካከል በተነሳው ግጭት ነው።
የኢራቅ ባለስልጣናት እንደሚሉት የሙክታዳ አል ሳድር ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ጥሰው ከገቡ በኋላ በርካቶች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
አለመረጋጋቱ የተቀሰቀው ሙክታዳ አል ሳድር ከፖለቲካው አለም ራሳቸውን ማግለላቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው።
የኢራቅ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚንስትር መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ ያደረጉ ሲሆን በሌሎች ከተሞች በተፈጠረውም አለመረጋጋት ጦሩ ብሔራዊ የሰዓት እላፊ አውጇል።
የኢራቅ ጎዳናዎች በተዋጊዎች የተኩስ ልውውጥ የተሞሉ ሲሆን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከታየውም አስከፊው ነው ተብሏል።
እነዚህ ውጊያዎች የተካሄዱት በከተማው አረንጓዴ ዞን ተብሎ በሚጠራውና የመንግሥት ህንፃዎች ችና የውጭ ኤምባሲዎች በሚገኙበት አካባቢ ነው።
ግጭቱ የተፈጠረው ለሙክታዳ አል ሳድር ታማኝ በሆኑት ፒስ ብርጌድስ በተሰኘው ሚሊሻ እና በኢራቅ ጦር አባላት መካከል እንደሆነ የኢራቅ ደህንነት ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች አንዳንድ ተዋጊዎች በሮኬት የሚንቀሳቀሱ የእጅ ቦምቦችን ጨምሮ የከባድ መሳሪያ ልውውጥ እንደነበር ያሳያሉ።
ይህንንም ተከትሎ ኢራን ከኢራቅ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር የዘጋች ሲሆን ኩዌት ዜጎቿ አገሪቷን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች።
የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት 15 የሙክታዳ አል ሳድር ደጋፊዎች በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ሲያልፍ ወደ 350 የሚጠጉት ተቃዋሚዎች ቆስለዋል ሲል ኤኤፍኢ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ቃለ አቀባይ በኢራቅ የተከሰቱት ሁነቶች አስደንጋጭ መሆናቸውን ገልጻው “ሁከቱን ለማረጋጋት አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ” ጥሪ አቅርበዋል ።
ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሙክታዳ አል ሳድር አጋር የሆኑት ሙስጠፋ አል ካዲሚ የካቢኔ ስብሰባዎች እንዲታገዱ ውሳኔ አሳልፈው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሃይማኖት አባቶች ጣልቃ እንዲገቡ እና ብጥብጡን እንዲያቆሙ ተማጽነዋል።
የሙክታዳ አል ሳድር ከፍተኛ ረዳት ለኢራቅ መንግስት የዜና ወኪል ኢ ኤን ኤ እንደተናገሩት ሁከቱ እና የጦር ውጊያው እስኪቆም ድረስ የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ሙክታዳ አል ሳድር ራሳቸውን ከፖለቲካ ህይወት ለማግለል ውሳኔ ያስተላለፉትተቀናቃኝ የሺአ መሪዎች እና ፓርቲዎች የኢራቅን የፖለቲካ ስርዓት ለማሻሻል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው።
በጥቅምት ወር፣ ለሙክታዳ አል ሳድር ታማኝ የሆኑ እጩዎች በኢራቅ ፓርላማ ብዙ መቀመጫዎችን ቢያሸንፉም ነገር ግን መንግስት ለመመስረት በቂ መቀመጫዎችን ማግኘት አልቻሉም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኢራን ከሚደገፉ የሺዓ ቡድኖች ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ባለመሆናቸውም ለአንድ አመት ያህል የፖለቲካ አለመረጋጋት አስከትሏል።
ሙክታዳ አል ሳድር የኢራቅ ፖለቲከኛ እና የሚሊሺያ መሪ ሲሆኑ የሳድሪስት ንቅናቄ መሪ እንዲሁም ቀደም ሲል የአሜሪካ ጦር ኢራቅ ውስጥ በነበረበት ወቅት ይመሩት የነበረው ሚሊሻ ማህዲ ጦር ተተኪ የሆነው የሰላም ኩባንያዎች መሪ ናቸው።