በመንትያ ቄሶች እና በመንትዮች ታጅበው የተዳሩት መንትዮች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አራት መንትዮችን የሚያሳየው ፎቶ በደቡባዊ ሕንድ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኗል።

ምሥሉ ሁለት መንትያ ወንድማማቾች መንትያ እህትማማቾችን ማግባታቸውን ያሳያል። መንትዮቹን ያጋቡት ደግሞ መንታ ካህናት ሲሆኑ ያጀቧቸውንም መንትያ ታዳጊዎች ናቸው።

ይህ ለየት ያለ እና ብዙዎችን ያስደመመ የሰርግ ሥነ ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ የታሰበበት እና የታቀደ ነበር።

ከሙሽሮቹ አንዱ የሆነው አክሂል ቶማስ "ሁለት ጥንድ መንትያ ሙሽሮችን በአንድ ሰርግ ላይ ማግኘት አጋጣሚ ሊሆን አይችልም" ብሏል።

የአክሂል መንትያ ወንድም የሆነው ሙሽራው ኒክሂል ቶማስ "መንትዮችን ለማግባት ቆርጠን ነበር። ቤተሰባችን ለእኛ ተስማሚ የሆኑ ሙሽሮችን ለመፈለግ ሦስት ዓመታት ፈጅቶበታል" ይላል።

32 ዓመት የሆናቸው ወንድማማቾች በአካባቢው ባሕል መሠረት ትዳር ለመመሥረት ዘግይተዋል።

"በሠላሳዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ስለሆንን፣ ዘመዶቻችን መንትዮችን እንዳንጠብቅ አጥብቀው ይጠይቁን ነበር" ያለው አክሂል "ሌሎች [መንትያ ያልሆኑ] ሴቶችን ካላገባን ጨርሶ ላናገባ እንደምንችል አስጠንቅቀውናል" ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።

ቤተሰቦቻቸው ለልጆቻቸው ተስማሚ የሆኑ ሙሽሮችን ለማግኘት ተስፋ በማድረግ፣ በተለይ ለመንትዮች የሚሆን የሰርግ ሥነ ሥርዓት አዘጋጅተዋል።

አክሂል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከማጂ እና ከማሪያ ሜሪ ጋር ከመተዋወቃቸው በፊት እስከ 40 የሚደርሱ መንትያ እህቶችን እንዳገኙ ይናገራል። ዕጣ ፈንታ ሆኖ የ31 ዓመቶቹ እህትማማቾችም መንትያ ለማግባት ይፈልጉ ነበር።

"ከልጅነታችን ጀምሮ የምናገባ ከሆነ መንትዮች መሆን እንዳለባቸው ወስነን ነበር" ትላለች ማጂ።

"አክሂልን እና ኒክሂልን ስናገኛቸው ወዲያውኑ ወደድናቸው" ያለችው ማሪያ "የሕይወት አጋሮቻችን እንደሆኑ ወሰንን" ስትል ወዲያውኑ መስማማታቸውን ትናገራለች።

ከዚያም እህትማማቾቹ የሰርጋቸውን ሥነ ሥርዓት መንትያ ካህናት እንዲያከናውኑላቸው እንደሚፈልጉ ገለጹ።

ይህ ሀሳብ የመጣው ማጂ እና ማሪያ ባለፈው ዓመት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ መንትያ የሆኑትን ዲያቆናት፣ ጄሮን እና ጆሃን ጄምስን ካዩ በኋላ ነው።

ጋብቻው ከታቀደ በኋላ ወንድማማቾቹን አግኝተው በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲሳተፉ ጋበዟቸው።

የአክሂል እናት ከጥቂት ወራት በፊት በቤተ ክርስቲያን የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ መንትያ ካህናትን አይተው ስለነበር አጆ ፔሩምካትቲልን ሰርጉን እንዲያከናውኑላት አናጋገረቻቸው።

"ካህናቱን አግኝቼ ዝርዝሮቹን ስነግራቸው በጣም ተደሰቱ" ይላል አክሂል።

የሰርጉ ፎቶዎች በስፋት ከተጋሩ ጊዜ ጀምሮ መንትዮቹ ካህናት በጣም ደስተኞች ናቸው።

አጆ "ለእኛ፣ በእውነቱ የማይረሳ ሰርግ ሆኗል" ብለዋል።

ፎቶዎቹ በበይነ መረብ ላይ መዘዋወር ከጀመሩ ወዲህ ሁለት ሌሎች ቤተሰቦች የመንትያ ልጆቻቸውን ሰርግ እንዲያስፈጽሙላቸው ለካህናቱ ጥያቄ አቅርበዋል።

"የእኛ በፍቅር ተሳስበን የተገናኘን አይደለንም፤ በወላጆቻችን የታቀደ እና የተዘጋጀ ጋብቻ ነው" ይላል ኒክሂል ቶማስ።

ይህ ትዳር ወላጆች እና ዘመድ አዝማድ ተስማሚ የትዳር አጋርን ለመምረጥ በሚያግዙበት ባሕላዊ የሕንድ የጋብቻ ሥርዓት ነው።

የሰርጉ ፎቶዎች በስፋት ከተሠራጩ ወዲህ፣ ጥንዶቹ በበይነ መረብ ላይ ብዙ ምርቃትን ተቀብለዋል።

ብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንኳን ደስ አላችሁ ሲሏቸው፣ ሌሎች ደግሞ ለመንትዮች ድንቅ የሆነ ሰርግ ሲሉ ገልጸውታል።

"የሰርጋችን ፎቶዎች እንዲህ ተወዳጅ ይሆናሉ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር" ትላለች ማሪያ።

"ይህንን ያደረግነው ዝና ለማግኘት ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ ትኩረትን ለመሳብ አይደለም። ይህ የምናልመው ጋብቻ ነበር እና በድንገት ሰፊው ማኅበረሰብ ጋር ደርሷል" ትላለች።