ከጋዛ የተነሱ ካይቶች መገኘታቸውን ተከትሎ እስራኤል “ኃይል የተሞላበት” እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች
እስራኤል፣ ሐማስ ከጋዛ ግዛት በኩል ካይት፣ ድሮን እና ፊኛዎችን ሊልክ ይችላል በሚል ጋዛ ውስጥ የምትፈጽመውን ጥቃት እንደምታጠናክር አስጠነቀቀች።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጋዛ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የእስራኤል መንደር ውስጥ ፈንጂ ያልያዙ በራሪ ካይቶች መገኘታቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ዛሬ ሰኞ በሰጡት መግለጫ "ይህንን ክስተት ለማስቆም ኃይል የተሞላባቸው እርምጃዎች ይወሰዳሉ” ብለዋል።
የጋዛ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ፈንጂ የጫኑ ፊኛዎች (ባሉን) ወደ እስራኤል ተልከው ነበር። ፈንጂው ጫካ እና እርሻ ውስጥ እሳት አስነስቷል።
ሐማስ አሁን ወደ እስራኤል ገብተዋል የተባሉት ካይቶች የእርሱ አለመሆናቸውን በመግለጽ አስተባብሏል። በጋዛ “ፍርስራሾች ውስጥ ንጹህ ልጅነታቸውን የሚፈልጉ ሕፃናት” የሚጫወቱቸባው እንደሆኑም ጠቅሷል።
በተጨማሪም ቡድኑ እስራኤል ባለፈው ጥቅምት ላይ የተፈረመውን ተኩስ አቁም በመጣስ የምትፈጽመውን የአየር ጥቃት ለመቀጠል የእነዚህ ካይቶች ጉዳይ “በምክንያትነት” እየተጠቀመች ነው ሲል ከስሷል።
ባለፈው ሳምንት አርብ እና ቅዳሜ ላይ ከጋዛ ድንበር 800 ሜትር ርቀት ላይ ባለው ‘ኪቡዝ ናሃል ኦዝ’ የተባለ መንደር ውስጥ አራት ካይቶች ተገኝተዋል። ከዚያ በፊትም በደቡባዊ እስራኤል ሌሎች ስፍራዎችም ተጨማሪ ካይቶች መገኘታቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
መገናኛ ብዙኃኑ የጠቀሷቸው ወታደራዊ ምንጮች፣ ወደ እስራኤል ከገቡት ካይቶች ጀርባ የሐማስ እጅ እንዳለ እና በራሪዎቹን የላከውም እስራኤል ምን ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጥ ለመፈተን እንደሆነ ያምናሉ።
እነዚህ ካይቶች ላይ ግን ምንም አጠራጣሪ ቁስ አለመገኘቱን እና ስጋት እንደማይጋርጡ ወታደራዊ ምንጮቹ ገልጸዋል።
ይሁንና የመከላከያ ሚኒስትሩ ኢዝራኤል ካትዝ፣ “ምንም ትዕግስት” እንደማይኖር ተናግረዋል። “ባሉን የሚታየው እንደ ካይት ነው፤ ካይት ደግሞ እንደ ድሮን፤ ፈንጂ ኖረውም አልኖረውም” ብለዋል።
ሐማስ በበኩሉ ከእስራኤል በኩል የሚሰማው “ውንጀላ እና ዛቻ አደገኛ” እንደሆነ አስጠንቅቋል። ካይቶቹ “ከተፈናቃይ ካምፕ የመጡ የሕጻናት መጫወቻ” እንደሆኑም ገልጿል።