ተደፍራ ለተገደለችው ሄቨን የተጠራው የሻማ ማብራት እና መግለጫ በፖሊሶች ተቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, social Media
በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍራ ለተገደለችው የሰባት ዓመቷ ሕጻን ሄቨን አወት አርብ ነሐሴ 17/ 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኘው ኢሊሊ ሆቴል ሊደረግ የነበረው የመታሰቢያ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት እና ጋዜጣዊ መግለጫ በፖሊስ እንዲቋረጥ ተደረገ።
ለሄቨን አወት ፍትህን የሚጠይቀው ይህ ፕሮግራም ጋዜጣዊ መግለጫው በተጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በፖሊስ መቋረጡን በሴቶች እና ሕጻናት መብቶች ላይ የሚሠራው ሴታ ሴት ፓወር የተሰኘ የንቅናቄ ቡድን መሥራች እና ፕሬዚዳንት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴቶች ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት ምክትል ፕሬዚዳንት ቤተልሔም አካለወርቅ ለቢቢሲ ገልጻለች።
ሕጻኗን ለማሰብ እና ፍትህን ለመጠየቅ በኢሊሊ ሆቴል አርብ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ የተጠራው ይህ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ 57 ያህል ሰዎች ተገኝተው እንደነበር ቤተልሔም ትናገራለች።
ሆኖም ጋዜጣዊ መግለጫውን እንዲቋረጥ እና ጋዜጠኞች እና ተሳታፊዎች የቀረጿቸውን ቪዲዮዎች ፖሊሶች በር ላይ ቆመው ሲያስጠፉ እንዲሁም ስልክ መንጠቅ እና ሌሎች ማንገላታቶች እንደተፈጸሙም አስረድታለች።
ይህንን ዝግጅት ያዘጋጁት አካላት ለሁለት ሰዓታት ያህል ተይዘው እንደነበር ለሄቨን ድጋፏን ለመግለጽ በስፍራው ላይ ተገኝታ የነበረችው ቤተልሔም ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ መበተናቸውን ተናግራለች።
የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓቱን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቀንጅት፣ የኢትየጵያ ሴቶች መብት ተሟጋቾች፣ የሴቶች ማረፊያ እና ልማት ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ናቸው።
የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓቱ ፍትህ ለሄቨን አወት፣ በሴቶች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ነበር።
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ በስፍራው መሳሪያ የያዙ ፖሊሶች፣ ፌደራል ፖሊሶች እንደነበሩና ከፍተኛ ወከባ እንደነበር ለቢቢሲ አስረድታለች።
የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓቱ እና ጋዜጣዊ መግለጫ የተቋረጠው “ፍቃድ ባለመጠየቁ እንደሆነ” ከአዘጋጆቹ መስማቷን ቤተልሔም ለቢቢሲ ገልጻለች።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሄቨንን እንዲሁም ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንደሚታገሉ የምትናገረው ቤተልሔም ፖሊሶቹ ለተሳታፊው የገለጹት ነገር እንደሌለ አስረድታለች።
ቢቢሲ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ እንዲቋረጥ የተደረገበትን ምክንያት ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከፌደራል ፖሊስ ማብራሪያ ለመጠየቅ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ሄቨንን በመድፈር በዘግናኝ ሁኔታ የገደላት የሦስት ልጆች አባት ጌትነት ባዬ የተበየነበት ፍርድ በአገሪቱ ውስጥ ቁጣን እንዲሁም ውግዘትን ፈጥሯል።
መደፈሩ እና ግድያው የተፈጸመው ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ውስጥ ቢሆንም በበርካቶች ዘንድ የተሰማው በቅርቡ ነው።
ሕጻኗ ተደፍራ፣ እንዳትጮህ አፏ ውስጥ አሸዋ ተጨምሮባት፣ ታንቃ እንዲሁም ሰውነቷ ተተልትሎ ደጃፍ ላይ ተጥላ ነበር የተገኘችው። የሕጻኗን ሕይወት በዚህ አሰቃቂ መንገድ የነጠቀው ጌትነት 25 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ግለሰቡ ይግባኝ መጠየቁን ተከትሎ እናቷ ጉዳዩን ወደ ወደ መገናኛ ብዙኃን ይዛው የመጣች ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሕጻኗ ግድያ ዙሪያ ከባድ ቁጣ እና ሐዘን የተፈጠረ ሲሆን፣ ይህንን ለመግለጽ በተጀመረው የበይነ መረብ ፊርማ ማሰባሰብ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ፊርማቸውን አኑረዋል።












