ዩኬ ለጥገኝነት ጠያቂዎች በሩዋንዳ አዘጋጅታው የነበረውን ማረፊያ ጀርመን ልትጠቀምበት እንደምትችል ተጠቆመ

ባለፈው ዓመት የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱኤላ ብሬቨርማን በሩዋንዳ የተገነባውን የስደተኞች ማረፊያ ሲጎበኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱኤላ ብሬቨርማን በሩዋንዳ የተገነባውን የስደተኞች ማረፊያ ጎብኝተዋል።
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጥገኝነት ጠያቂዎች በሩዋንዳ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በዩኬ የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጁ መሠረተ ልማቶች ጀርመን ልትጠቀምበት እንደምትችል የአገሪቷ የስደት ስምምነቶች ኮሚሽነር ጠቆሙ።

የገዥው ጥምር መንግሥት አካል የሆነው ፍሪ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኛ ጆኦቺም ስታምፕ፣ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የተዘጋጀውን ማረፊያ ጀርመን ልትጠቀምበት እንደምትችል አመልክተዋል።

ሆኖም የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ቀደም ብሎ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ማመልከቻዎች ከአገር ውጭ ማስተናገድ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ የገለጹ ሲሆን፣ሃሳቡም ወደፊት ሊራመድ እንደማይችል ተናግረው ነበር።

አዲሱ የዩኬ መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ በቀድሞው ወግ አጥባቂ መንግሥት ተይዞ የነበረውን እቅድ መሰረዙ ይታወሳል።

እቅዱ በሕገ ወጥ መንገድ በትንንሽ ጀልባዎች የእንግሊዝ ቻነልን አቋርጠው ወደ አገሪቷ የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቆም ያለመ ነበር።

ስታምፕ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ በዩኬ የጀርመን አምባሳደር የሆኑት ሚጌል በርገር፣በተሰረዘው የዩኬ እቅድና ስደተኞችን በተመለከተ በጀርመን በተካሄደው ውይይት መካከል ልዩነት መኖሩን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በጀርመን ያለው ውይይት በሦስተኛ አገር ያሉ የጥገኝነት ጥያቄ ማመልከቻዎችን በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ እና በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ስለማስተናገድ መሆኑን በማስረዳት፣ “የጀርመን መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ የለውም።” ብለዋል።

በዩኬ ተይዞ የነበረው እቅድ ጉዳያቸውን በሦስተኛ አገር ሆነው እንዲከታተሉ ወደ ሩዋንዳ የሚላኩ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገሪቱ እንዲመለሱ የሚፈቅድ አልነበረም።

ስደተኞቹ ጥያቄያቸው በሩዋንዳ ተቀባይነት ካገኘ እዚያው እንዲቆዩ ሊፈቀድላቸው የሚችል ሲሆን ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካላገኘ ደግሞ እዚያው ለመቆየት ማመልከቻ ማስገባት አልያም በሌላ አገር ጥገኝነት ለመጠየቅ ማመልከት የሚያስችል ነበር።

ልክ እንደ ዩኬ ሁሉ የጀርመን መንግሥትም በተለይ ፀረ ስደት አቋም ያለው ቀኝ አክራሪ ፓርቲ በምርጫው ድል ከቀናው በኋላ ሕገ ወጥ ስደትን እንዲያስቆም ግፊት እየተደረገበት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስደትን የተመለከቱ ስምምነቶች የበርሊን ልዩ ተወካይ የሆኑት ስታምፕ ሐሙስ ዕለት በተካሄደ ውይይት ላይ እንደተናገሩት እቅዱ የአውሮፓ ሕብረትን ምሥራቃዊ ድንበር ተሻግረው የሚገቡትን ዒላማ ሊያደርግ የሚችል እና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ዩኤንኤችሲአር ክትትል የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ስታምፕ ጨምረውም “አሁን ላይ ከሩዋንዳ በስተቀር ይህንን ለማስፈፀም የፈቀደ ሦስተኛ አገር የለም” ብለዋል።

ኅዳር ወር ላይ ቻንስለር ሾላዝም የጥገኝነት ጥያቄ ማመልከቻዎችን ከውጭ አገር ማስተናገድ ይቻል እንደሁ ለማጣራት ቃል ገብተው የነበረ ሲሆን እንዲህ ዓይነት እቅድ ለማስፈፀም ግን ሕጋዊ ጥያቄዎች እንዳሉም አስጠንቅቀው ነበር።

የስታምፕን አስተያየት ተከትሎ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ከሌሎች አገራት ጋር በሚደረግ ውይይት ላይ አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል።

“ ሌሎች አገራት የሚከተሏቸው ፖሊሲዎች የራሳቸው ጉዳይ ነው። ሩዋንዳን በሚመለከት ያለን አቋም የሚታወቅ ነው።” ብለዋል በደፈናው።

የዩኬው ሌበር ፓርቲ የቀድሞውን መንግሥት የሩዋንዳ እቅድ “ ውድ” ሲል በምርጫ ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ ሰርዞታል።

ወግ አጥባቂው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊይም የሌበር ፓርቲ የመጀመሪያ እርምጃ የሩዋንዳውን እቅድ ማስወገድ እንደነበር ተናግረዋል።

“ አሁን ላይ የገነባነውን ማረፊያ ጀርመን ልትጠቀምበት ትፈልጋለች” ሲሉም የሌበር የኢምግሬሽን ፖሊሲዎች እየጠቀመ ያለው ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እና የአውሮፓ ሕብረትን ብቻ ነው ብለዋል።

ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ የዩኬ እቅድ በፍርድ ቤት ታግዶ የነበረ ሲሆን በእቅዱ መሠረት ወደ ሩዋንዳ የተላከ ስደተኛ የለም።

ሆኖም በዩኬ የገንዘብ ድጋፍ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ የስደተኞች ማረፊያ ተገንብቷል።

ሚያዚያ ወር ላይም የአንድ ሆስቴል ሥራ አስኪያጅ ሆስቴሉ ሰዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

እቅዱ መሻሩን ተከትሎም የዩኬ መንግሥት እቅዱን ለማስፈፀም ለሩዋንዳ የከፈለውን 310 ሚሊዮን ዶላር ማስመለስ ይችል እንደሆነ እየመረመረ እንደሆነ ገልጾ ነበር።

የሩዋንዳ መንግሥት ግን ገንዘቡን ለመመለስ የሚያስገድድ ምንም ዓይነት ሕግ የለም ብሏል።