ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፍጋኒስታን በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አንድ ሺህ ሰዎች ሞቱ
በአፍጋኒስታን በደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አንድ ሺህ ሰዎች ሲሞቱ አንድ ሺህ አምስት መቶ ደግሞ መቁሰላቸውን የታሊባን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ከደረሰበት የምስራቅ ፓክቲካ ግዛት የወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት መሬቱ ተደርምሶ እንዲሁም በጭቃ የተሰሩ ቤቶችም ፈራርሰው ነው።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም ጉዳት የደረሰባቸውን ለማከም እየጣሩም ነው ተብሏል።
ራቅ ባሉ አካባቢዎች ሄሊኮፕተሮች ተጎጂዎችን ወደ ሆስፒታል እያደረሱ ይገኛሉ።
የታሊባን መሪ ሂባቱላህ አክሁንዝዳ እንደገለጹት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመዋል የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር ይችላል።
የፓኪቲካ ግዛት የመረጃ ሃላፊ መሀመድ አሚን ሀዚፊ አንድ ሺህ ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም አንድ ሺህ አምስት መቶ መቁሰላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህም በአፍጋኒስታን ውስጥ በሃያ አመታት ውስጥ ከታየው አስከፊው የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሆነም ተገልጿል።
ርዕደ መሬቱ ከደቡብ ምስራቅ ክሆስት ከተማ 44 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ የተከሰተ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ተኝተው በነበረበት ወቅት ላይ ነው።
"ባለፍንበት መንገድ ሁሉ በርካታ የሚወዷቸውን እንዳጡና ሃዘን ላይ እንደሆኑ እየሰማን ነው። ቤቶች ፈራርሰዋል" በማለት ክፉኛ በርዕደ መሬቱ በተመታችው የፓኪቲካ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በአፍጋኒስታን በገጠራማ አካባቢዎች ያሉ መኖሪያ ቤቶች ያልተረጋጉ ወይም በደንብ ያልተገነቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።
አደጋውን ተከትሎ የስልክ መስመር ማማዎች ላይ በደረሰ ጉዳት የመገናኛ ዘዴዎች የተቋረጠ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል በአካባቢው የሚኖር ሌላ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ብዙ ሰዎች ስልካቸው ስለማይሰራ ስለ ዘመዶቻቸው ደህንነት አያውቁም። ወንድሜ እና ቤተሰቡ ሞተዋል። እኔም የተረዳሁት ከበርካታ ሰአታት በኋላ ነው ብዙ መንደሮች ወድመዋል።" ብሏል ጋዜጠኛው