ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሕብረቱ ሊቀ መንበር የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት አፍሪካውያንን እንደጎዳ ተናገሩ
የሴኔጋል ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የሆኑት ማኪ ሳል፣ አፍሪካ በዩክሬን እና በሩሲያ ጦርነት ተጎጂ በመሆናቸው የገጠማቸውን ችግር ለማቅለል እንዲያግዙ የሩሲያውን መሪ ቭላድሚር ፑቲንን ጠየቁ።
ሁለቱ መሪዎች በደቡባዊቷ የሩሲያ ከተማ ሶቺ በተወያዩበት ወቅት የሩሲያው ፕሬዝዳንት በእህልና በማዳበሪያ ምርት አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለማቅለል ቃል የገቡ ቢሆንም በዝርዝር አልተናገሩም።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ጨምረውም ሩሲያ በዩክሬን ወደቦች በኩል የእህል ምርቶች ወደ ሌሎች አገራት እንዳይሄዱ አግደዋል መባሉን አስተባብለዋል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በአፍሪካ ጥቅም ላይ ከሚውለው የስንዴ ምርት ውስጥ 40 በመቶው ከሩሲያ አሊያም ከዩክሬን የሚመጣ ነበር።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በጥቁር ባሕር ላይ የሚገኙት የዩክሬን ወደቦች ሥራ በማቆማቸው ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ማስተናገድ አቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አሚን አዋድ "ወደቦቹ እንዲከፈቱ ካልተደረገ ረሃብ ሊከሰት ይችላል" ብለዋል።
ጨምረውም የእህል አቅርቦት እጥረቱ 1.4 ቢሊዮን ሕዝብን ለችግር የሚዳርግ በመሆኑ የጅምላ ስደትን ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።
ጦርነቱ በአፍሪካ በምርት መታጣትና በግጭቶች ምክንያት ያለውን የምግብ እህል አቅርቦት ችግርን የበለጠ አባብሶታል።
በአፍሪካ ውስጥ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ ውስጥ ከ80 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች አስከፊ የምግብ እጥረትና ረሃብ እንደተጋረጠባቸው የዓለም ምግብ ፕሪግራም ኃላፊ ማይክ ደንፎርድ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ሳል ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን “ምንም እንኳን የአፍሪካ አገራት ከግጭቱ ስፍራ ርቀው ቢገኙም፣ ጦርነቱ ባስከተለው የምጣኔ ሀብት ተጽእኖ ሰለባ ሆነዋል” ሲሉ እንደነገሯቸው ጠቅሷል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በውይይታቸው ሩሲያ ተቆጣጥራቸው በሚገኙት የአዞቭ የጥቁር ባሕር ወደቦች በኩል የዩክሬን የእህል ምርቶች ያለ ችግር እንዲወጡ እንደሚፈቅዱ ተናግረዋል።
ጨምረውም የተሻለው መፍትሔ የሚሆነው የሩሲያ ወዳጅ በሆነችው በቤላሩስ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በማንሳት የእህል ምርቶች በዚያ በኩል እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
አንዳንድ ተንታኞች ሩሲያ የሚፈጠረውን የምግብ አቅርቦት ቀውስ በመጠቀም በምዕራቡ ዓለም ላይ ጫና ለማሳደር ትፈልጋለች ይላሉ።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጋር ተገናኝተው ከመወያየታቸው በፊት ሩሲያ “ሁልጊዜም ከአፍሪካ ጎን ናት” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን በአህጉሪቱ ስላለው የምግብ አቅርቦት ቀውስን በተመለከተ በግልጽ ያሉት ነገር የለም።
ሴኔጋልን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ውስጥ አንዱን ወገን ከመደገፍ የተቆጠቡ ሲሆን፣ ማኪ ሳልም የምግብ አቅርቦቶች ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ከጣሉት ማዕቀብ “ውጪ” መሆን አለባቸው ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለተከሰተው የምግብ ዋጋ መናር ምዕራባውያን ተጠያቂ ናቸው የሚለውን ክስ ውድቅ በማድረግ፣ ለችግሩ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሁለቱ መሪዎች በተገናኙበት ወቅት ነው ማኪ ሳል ለፑቲን ጦርነቱ አፍሪካን እየጎዳት መሆኑን የተናገሩት ሲል የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ ከሴኔጋል ከመነሳታቸው በፊት ጽህፈት ቤታቸው፣ የጉብኝታቸው አላማ በጦርነቱ ምክንያት በዩክሬን ወደቦች መንቀሳቀስ ያልቻለውን የእህል ምርትና የማዳበሪያ ክምችት እንዲጓጓዝ ለማስቻል ነው ብሎ ነበር።
በጦርነቱ ሳቢያ በተፈጠረው የዋጋ ንረት በተለይ የአፍሪካ አገራት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል።
ቀደም ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል የፕሬዝዳንት ፑቲን ቤተመንግሥት የሆነውን ክሬምሊንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ፑቲን የዩክሬን የእህል ምርት ምን እንዳጋጠመው በዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣሉ ብሎ ነበር።