ህንድ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ አረፈች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ህንድ ታሪካዊ በተባለ የጨረቃ ተልዕኮ ከጨረቃ አቅራቢያ በደቡብ ዋልታ በማረፍ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።
በዚህም ህንድ ከአሜሪካ፣ ሶቪየት ህብረትና ቻይና በመቀጠል ጨረቃ ላይ ያረፉ ጥቂት ሀገራትን ተቀላቅላለች።
ቻንድራአያን- 3 የተሰኘው ተልዕኮ በታቀደለት ሰዓት ጨረቃን ረግጧል።
ይህንንም ተከትሎ በህንድ ዙሪያ ዜጎች ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ “ህንድ አሁን ጨረቃ ላይ አለች” ብለዋል።
የብሪክስ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ ሆነው ሁነቱን የተከታተሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሌሎች ሀገራት መድረስ ያልቻሉቡት ቦታ ላይ ደርሰናል። ይህ የሚያስደስት ክስተት ነው” ሲሉም አክለዋል።
የህንድ የህዋ ምርምር ተቋም ኃላፊ ስሪዳራ ፓኒከር ሶማንታ ጨረቃ ላይ በስኬት ያረፍነው በኛ ስራ ብቻ ሳይሆን በተቋሙ ውስጥ ባለፉት ትውልዶች ነው ብለዋል።
የህንድ የተሳካ የጨረቃ ላይ ጉዞ ከመሰማቱ ጥቂት ቀናት ቀድም ብሎ የሩሲያ ሉና 25 የተሰኘ መንኮራኩር ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ጨረቃ ላይ መውደቁ ተዘግቦ ነበር።
የሩስያ መንኮራኩር መከስከስ በጨረቃ ደቡብ ዋልታ ላይ ማረፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያመላከተ ነው። ስፍራው “ወጣ ገባ”ና “በቁጥቋጦ” የተሞላ መሆኑ ለጨረቃ ተልዕኮ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በተመሳሳይ ሩሲያ ወደዚሁ ስፍራ ያደረገችው ጉዞ ፍሬ አላፈራም ነበር።
ህንድ ያደረገችው የጨረቃ ጉዞ ዋነኛ ዓላማዎች መካከል ውሃ ያዘለ በረዶማ አከባቢዎችን መፈለግ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። ይህ ግኝት ወደፊት ሰዎች በጨረቃ ላይ እንዲኖሩ ሊያስችል ይችላልም ይላሉ።
በተጨማሪም ወደ ማርስና ሌሎች በርቀት የሚገኙ ለሚገኙ መንኮራኩሮችም ግብአት ለማቅረብ እንደሚያግዝም ያስረዳሉ።
አምስት ሳይንሳዊ መሳሪያዎችን የያዘው የህንድ የጨረቃ ተልዕኮ የየጨረቃን ገጽታ ባህሪያት ለመረዳት ያግዛል።
ወደ ጨረቃ የተላከው መንኮራኩር የህንድን ሰንደቅ ዓላማና የህንድ የህዋ ምርምር ተቋም አርማ የያዙ ሲሆን በጨረቃ ላይ ምልክት እንደሚያኖሩ አንድ ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ቻንድራአያን- 3 የህንድ ሶስተኛው ተልዕኮ ሲሆን የቀድሙትን የጨረቃ ምርምሮች የሚያግዝ ነው።
የህዋ ምርምር ተቋሙ ባለስልጣናት እንደሚሉት ይህ ተልዕኮኢ “እጅግ ጠቃሚ” ሳይንሳዊ ግኝቶችን የሚያመጣ ነው።
ህንድ በተሳካ ሁኔታ ላይ ጨረቃ ላይ ያረፈችው ቻንድራአያን- 3 ጨረቃ ላይ ከመላኳ 15 ዓመታት አስቀድማ ቻንድራአያን- 1 እንደ አውሮፓውያኑ በ2008 ልካ ነበር።












