ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቱን አስታወቀ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለተጓዦች ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ ለመክፈትና ለሰብአዊ እርዳታ የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ለማደረግ መስማማቱን አስታወቀ።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ከአሜሪካው የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊና “ከሌሎች ወዳጅ ሀገራት” ጋር ንግግር ከተደረገ በኃላ ስምምነት ላይ መደረሱን ዛሬ በወጣ መግለጫ ላይ ገልጸዋል።
“ለሲቪል ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ ለመክፈትና የተጎዱትን ለማስወጣት ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ለ24 ሰዓት ተኩስ አቁም ይሁንታን ሰጥቷል” ብለዋል ሄምቲ።
የሱዳን ጦር በበኩሉ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተደርሶበታል ያለውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው በሚል ውድቅ አድርጓል።
“ከአሸማጋዮቹም ሆነ ከአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጋር ተኩስ ስምምነቱን በተመለከተ መቀናጀታቸውን አናውቅም። ሆኖም አማጺው ቡድን 24 ሰዓት የተኩስ አቁም ተደርሷል ብሎ ማወጁ በሰዓታት ውስጥ የሚደርስበትን አስከፊ ሽንፈት ለመሸፈን ያለመ ነው” ሲሉ የሱዳን ጦር ኃይል አቀባይ በጦሩ ትዊተር ገጽ አስፍረዋል
“ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የገባን ሲሆን ዋነኛ ጥረታችንም የታለመለትን የዘመቻ ዓላማ በማሳካት ላይ ያተኮረ ነው" ሲል የሠራዊቱ መግለጫ አክሎ ገልጿል።
ሁለቱ ሃይሎች ቀድሞ በመንግስታቱ ድርጀት አማካኝነት የደረሱትን የሰብአዊ እርዳታ የተኩስ አቁም ስምምነት አላከበሩም።
ቀድሞ በተመድ በኩል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ላለመከበሩ የሱዳንን ጦር ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን ወታደሮች “ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ ቦምብ ከአየር በማዝነብ የሲቨል ሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥለዋል” ሲሉም ወንጅለዋል።
“ይህ ድርጊትም ዓለም አቀፍ መርህዎችን እና ሰብአዊ ህጎቸን የጣሱ ናቸው” ሲሉም አክለዋል።
ይህንን የተኩስ አቁም የሱዳን ጦር ያጣጠለው ሲሆን በካርቱም እስከዛሬ ጠዋት ድረስ ውጊያ መቀጠሉ ተሰምቷል
አራተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የሱዳን ውጊያ 185 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ ከ1 ሺህ 800 የሚልቁ ሰዎች ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል።
በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላት መካከል እየተደረገ ያለው ፍልሚያ የቀጠለ ሲሆን የካርቱም ከተማም በአየር ጥቃትና በቀላል የቡድን መሳሪያዎች የታገዙ ውጊያዎችን እያስተናገደች ነው።
አገሪቷን ወደ ትርምስ ለመክተት ስጋት በደቀነው ግጭት መሃል ሁለት ጄነራሎች ተፋጠዋል።