ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩሲያ ጥቃት ሚሊዮኖች ከኃይል አቅርቦት ውጪ ሆነዋል ሲሉ ዜሌንስኪ ከሰሱ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በአውደ ውጊያዎች ያልተሳካላት ሩሲያ በኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ላይ “ሽብር” እየፈጸመች ነው ሲሉ ከሰሱ።
ሩሲያ በዩክሬን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ከኤሌትሪክ አቅርቦት ውጪ መሆኑንም ነው ዜሌንስኪ የገለጹት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ላይ መጠነ ሰፊ የሰው አለባ አውሮፕላን (ድሮን) እና የሚሳኤል ጥቃቶችን እየፈጸመች ነው።
እነዚህ ጥቃቶች መሰንዘር የጀመሩት የሩሲያ ወታደሮች ኼርሶን ከተባለው ግዛት እንደሚወጡ በይፋ ከተናገረ በኋላ ነው።
ሩሲያ በአውደ ውጊያዎች ከባድ ሽንፈት ማስተናገዷን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከውጊያ ሜዳዎች ርቀው በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ያሉ የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶችን እያጠቃች ነው።
ባለፈው ወር ብቻ የአገሪቱ አንድ ሦስተኛ የኃይል ጣቢያዎች እንደ ወደሙ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ የዩክሬን መንግሥት ዜጎቹ ኤሌክትሪክን በቁጠባ እንዲጠቀሙ ለማሳሰብ ተገዷል።
“ወደ 4.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በጊዜያዊነት ከኃይል አቅርቦት ጋር ተቆራርጠዋል” ብለዋል ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ትላንት በሰጡት መግለጫ።
ጨምረውም በአውደ ውጊያ ድል ማግኝት ያቃታት ሩሲያ የኃይል አቅርቦት ማዕከላትን ኢላማ ማድረጓ “ደካማነት” ነው ብለዋል።
“ሩሲያ በኃይል አቅርቦት እየፈጸመች ያለችው ሽብር ጠላታችን እየተዳከመ መሆኑን ያሳል። ዩክሬንን በአውደ ውጊያ ልታሸነፍ አትችልም። ስለዚህ ሕዝባችንን በዚህ መልኩ ሊሰብሩት እያሰቡ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ የዜሌንስኪ ውንጀላ የተሰማው የሩሲያ ወታደሮች ከተቆጣጠሩት የኼርሶን ግዛት እየወጡ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች በተሰሙበት ጊዜ ነው።
ክስተቱም ሩሲያ የደረገችው ትልቅ ማፈግፈግ ነው ተብሏል።
ኼርሶን ውስጥ በሩሲያ የተቋቋመው አስተዳደር ውስጥ ባለሥልጣን የሆኑት ኪርል ስትሪሞሱቭ ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የሞስኮ ጦር አካባቢውን ለቆ ሊወጣ ይችላል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምዕራባውያኑ ባለሥልጣናት ደግሞ የሩሲያ ጦር አዛዦች ከአካባቢው መልቀቃቸውን ተናግረዋል።