ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ሩሲያ ግድቡን ለማፈንዳት እያሴረች ነው ሲሉ ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, MAXAR
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኘውን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለማፈንዳት እየተዘጋጀች ነው ሲሉ ከሰሱ።
ይህም ሁኔታ ወደ ከፍተኛ አደጋ ያመራል ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በዲኒፐር ወንዝ ላይ የሚገኘው የካሆቭካ ግድብ ላይ የሩሲያ ኃይሎች መሳሪያ መጥመዳቸውን አገራቸው ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክት ተናግረዋል።
ግድቡ በሩሲያ ይዞታ ሥር ቢሆንም የዩክሬን ኃይሎች እየተጠጉ ይገኛሉ።
ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን በካኮቭካ ግድብ ላይ ሚሳኤል ተኩሳለች በሚል ክስ አቅርባለች።
ግድቡ ሩሲያን በዲኔፐር ወንዝ በኩል በከፊል በቁጥጥር ስር ባለው ኬርሶን ክልል የሚያገናኛት አንዱ መንገድ ነው።
አርብ ዕለት ቁልፍ መሸጋጋሪያ በሆነችውና አንቶኒቭስኪ ድልድል ላይ ዩክሬን ባደረሰችው የሮኬት ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን በሩሲያ የተሾሙ የኬርሶን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ሩሲያ በዚህ ሳምንት በኬርሶን የሾመቻቸውን ባለስልጣናት ማስወጣት ጀምራለች። ከዚህ በተጨማሪም ከ50-60 ሺህ ነዋሪዎችም ለቀው እንደሚወጡ የተናገረች ሲሆን ይህ እርምጃም በዩክሬን ባለስልጣናት ዘንድ አስገዳጅ ማፈናቀል ነው በሚል ውግዘት ደርሶበታል።
በዩክሬን አዲሱ የሩሲያ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሰርጌይ ሱሮቪኪን በበኩላቸው የዩክሬን ሃይሎች በኬርሶን ከተማ እና በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቡ ላይ "የተከለከሉ የጦርነት ዘዴዎችን" ሊጠቀሙ እንደሚችሉ በመጥቀስ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ማስወጣት ነው ሲሉ ተከራክረዋል ።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ለአውሮፓ ህብረት መሪዎች ሃሙስ ዕለት በቪዲዮ እንደተናገሩት ሩሲያ መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ የዩክሬን የሃይል መሠረተ ልማት አውድማለች ብለዋል።
ይህም በክረምት ወራት በተቻለ መጠን በኤሌክትሪክ እና በማሞቂያ ላይ ችግሮችን ለመፍጠር ያለመ ነው ሲሉ ከሰዋል።
የሩስያ ወረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ዩክሬናውያን አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲጠቀሙ ተጠይዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ከጥዋቱ 1 ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ድረስ የአጠቃቀም ገደብ ወጥቷል።












