በኬንያ ሊደረግ የነበረው ከፍተኛ የአደባባይ ተቃውሞ ሰልፍ ተሰረዘ

ታትሟል

የፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን ጥሪ ተከትሎ በኬንያ ዛሬ ሰኞ ሊደረግ የነበረው ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰረዘ።

ተቃውሞው መሠረዙን ይፋ ያደረጉት ተቃውሞውን ሲጠሩ የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ናቸው።

ትናንት ማታ በቴሌቪዥን ንግግር ያደረጉት ኦዲንጋ ተቃውሞውን የሰረዝነው የፕሬዝዳንቱን ጥሪ ተከትሎ ‘ለንግግር ቦታ እንስጥ’ በሚል ነው ብለዋል።

ኦዲንጋ በሳምንት ሁለት ቀን ሰኞና ሐሙስ በመላው አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ የንብረት ውድመት እና የሰው ሕይወት ሕልፈት ተከትሏል።

ትናንት ምሽት ለሕዝባቸው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው ኦዲንጋ ሕገ መንገሥቱን እንዲያከብሩ ጥሪ አድርገው ነበር።

ሩቶ በተቃዋሚዎች የቀረበላቸውን ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን በአዲስ መልክ የማዋቀሩን ሐሳብ መቀለባቸው እየተነገረ ነው።

ተቃዋሚው ኦዲንጋ በመላ አገሪቱ የተከሰተውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው ወደ አደባባይ ወጥተው በመንግሥት ላይ ያላቸውን ቁጣ እንዲገልጹ ጥሪ አድርገው ነበር።

በዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ ከፍተኛ ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርሃት ተፈጥሮ ነበር።

የአገሪቱ የጋዜጠኞች ማኅበር ተቃውሞ መጠራቱን ተከትሎ መንግሥት ኢንተርኔት ሊዘጋ ይችላል የሚል መረጃ ደርሶኛል በሚል መግለጫ አውጥቶ የነበረ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሩቶ በምሽቱ ንግግራቸው ሚዲያ የምናፍንበት ኢንተርኔት የምንዘጋበት ዘመን ድሮ አልፏል፤ ኬንያ ብዙ ርቀት ተጉዛለች ሲሉ ሀሜቱን አጣጥለውታል።

ለፕሬዝዳንትነት አምስት ጊዜ ተወዳድረው ያልተሳካላቸው ኦዲንጋ በኬንያ ረዥም ዓመት በፖለቲካ ከፍተኛ ኃላፊነት የቆዩ መሪ ሲሆኑ በአንድ ወቅት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

ኦዲንጋ ትናንት ምሽት ተቃውሞ መሰረዙን ባወጁበት ንግግራቸው ከፕሬዝዳንት ሩቶ ጋር የሚደረገው ንግግር ፍሬ ካላፈራ ሕዝቡን በድጋሚ ለተቃውሞ እንደሚጠሩ አስጠንቅቀዋል።