መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባቸው የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪ ከስልጣን ለመልቀቅ ተስማሙ

ታትሟል

በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ጨብጠው የነበሩት እና ባለፈው አርብ ከስልጣን በመፈንቅለ መንግሰት የተባበሩት የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪ ከስልጣን ለመውረድ መስማማታቸውን የሃይማኖት እና ማህበረሰብ መሪዎች ገለጹ።

የቀድሞውን ወታደራዊ መሪ ሌተናል ኮኖሬል ፖል ኤነሪ ዳይምባ ራሳቸውን የሀገሪቱ አዲስ መሪ አድርገው ላወጁት ካፒቴን ኢብራሂም ትሬዎር ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸውንም ተናግረዋል።

ይህ ዜና የተሰማው የቀድሞ የሀገሪቱ መሪ ሌተናል ከነሬል ዳምቢያ እንደመሸጉበት በተነገረው የፈረንሳይ ወታደራዊ ሰፈር ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ነው።

አርብ የተደረገው መፈንቅለ መንግሥት በዘንድሮው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው።

ሁለቱም መፈንቅለ መንግሥት ሲፈጽሙ እንደምክንያት የቀረበው በሀገሪቱ ያሉት መሪዎች በሀገሪቱ ጸጥታን ማስከበር አልቻሉም የሚል እና ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት አልቻሉም በሚል ነው።

የቡርኪናፋሶ መንግሥት የሀገሪቱን ከ60 በመቶ በታች ያለ ግዛት ብቻ የሚቆጣጠር ሲሆን እስላማዊ ታጣቂዎች እያደረሱ ያለው ጉዳት እየከፋ እንደሄደ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአፍሪካ ህብረት በሀገሪቱ በአውሮፓውያኑ ሃምሌ 2023 ህገ መንግሥቱን መሰረት ያደረገ አመራር ወደ ስልጣን እንዲመጣ ጠይቋል።

የዚህ ጥያቄ መነሻ ያደረገው በመፈንቅለ መንግሥት የተባረሩትን የቡርኪናፋሶ መሪ ህገ መንግስታዊ አይደሉም በሚል የምእራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ የደረሰበትን ስምምነት ተከትሎ ነው።  

ኢኮዋስ ቀደም ብሎ በሀገሪቱ የሲቪል አመራር ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መፈንቅለ መንግሥት መከናወኑ “ተገቢ አይደለም ሲል” ኮንኖት ነበር።

በቀድሞ የወታደራዊ መሪ ሌተናል ኮኖሬል ዳይምባ በቀጥታ የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም  የሃይማኖት እና የማህበረሰብ መሪዎች ግን ሰውዬው ከስልጣን ለመውረድ ሃሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።  

“ከፍተኛ የሰው እና የንብረት ጉዳት የሚያስከትል ግጭትን ለማስቀረት” ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸው መሪዎቹ ተናግረዋል ሲል የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ጨምረውም ሌተናል ኮኖሬል ዳይምባ ከስልጣን ለመውረድ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።

ይህም ለጥበቃቸው ዋስትና እንዲሰጣቸው፣ በእርቅ ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ እና በሁለት በአመት ውስጥ የሲቪል መንግሰት በሀገሪቱ እንዲቋቋም የተደረሰው ስምምነት እንደሚፈጸም ማረጋገጫ ይሰጠኝ የሚለውን ያጠቃልላል።

በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት ሌተናል ኮኖሬል ዳይምባ ከሳቸው በፊት የነበሩትን ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬ በሀገሪቱ ስጋትነቱ እየጨመረ የመጣውን የእስላማዊ ታጣቂ ጉዳይ አያያዝ አልተሳከላቸውም በሚል በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከስልጣን አስወግደዋቸዋል።

በዚህም ሳቢያ በሃገሪቱ ያሉ በርካታ ዜጎች ደህንት ሳይሰማቸው ቆይቷል።

በሀገሪቱ የእስላማዊ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ብቅ ያለው በአውሮፓውያኑ 2015 ሲሆን በሺዎች የሚቇጠሩ ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ እና ከ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አስገድዷል።

 ቡርኪናፋሶ ነጸነቷን ካገኘችበት ከአውሮፓውያኑ 1960 ወዲህ ስምንት መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባታል።