የሩሲያ ጦር ቁልፍ ከሆነችው የዩክሬን ከተማ እንዲያፈገፍግ ተደረገ

ታትሟል

ሩሲያ ወታደሮቿን ቁልፍ ከሆነችው የዩክሬን ሊማን ከተማ አስወጥታለች።

ይህም እርምጃ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ለምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ ትልቅ ሽንፈት ነው ተብሏል።

ሩሲያ ወታደሮቿን እንዲያፈገፍጉ ያደረገችው በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿ በከተማዋ ሊከበቡ ነው በሚል ስጋት እንደሆነ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሊማን ከተማን መልሶ መቆጣጠር ለዩክሬን ስልታዊ ጠቀሜታ አለው ተብሏል።

ከተማዋ የሩሲያ የሎጂስቲክ ማዕከል ሆና ያገለገለች ሲሆን የዩክሬን ወታደሮች በዶኔትስክ እና በሉሃንስክ ክልሎች ውስጥ ተጨማሪ ግዛቶችን ለመቆጣጠር በር እንደምትከፍት ተገልጿል።

በኢንተርኔት ላይ የተጋሩ የቪዲዮ ምስሎች በከተማዋ ዳርቻ ላይ የዩክሬን ወታደሮች ሰንደቅ አላማቸውን ሲያውለበልቡም ታይቷል።

ምንም እንኳን ሰማያዊ እና ቢጫ ቀለም ያላቸው የዩክሬን ሰንደቅ አላማዎች በሊማን ከተማ መውለብለብ ቢችሉም ውጊያው አሁንም እንደቀጠለ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ተናግረዋል።

ሆኖም ፕሬዚዳንቱ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

በሊማን የገጠመው የጦር ሜዳ ሳንካ የቺቺንያ መሪና ቀንደኛው የሩሲያ ደጋፊ ራምዛ ካድሮ ሩሲያ እንዲህ አይነት ሽንፈር ሲገጥማት ውስን በሆነ መልኩ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን መጠቀም አለባት ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የሊይማን ከተማ በዶኔትስክ የግዛት ክልል ውስጥ ትገኛለች። የዶኔትስክ ግዛት ሩሲያ አርብ እለት ወደ ግዛቷ ይቀላቀላሉ ብላ ካወጀችባቸውና አራት በከፊል ከተያዙ የዩክሬን ክልሎች አንዱ ነው። ይህንን ውሳኔ ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮች ህገወጥ የመሬት ወረራ ሲሉ አጣጥለውታል።

የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር አማካሪ ቀደም ሲል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከቀናት ከባድ ውጊያ በኋላ በቅርብ ጊዜ በሊማን ዙሪያ የተመዘገቡ ግስጋሴዎች እየታየ ያለውን ስኬት የሚወክል ነው ብለዋል።

የሩሲያ ተዋጊዎች እጅ እንዲሰጡ እድል መሰጠቱን የተናገሩት ዩሪክ ሳክ ከሩሲያ ጦር አመራሮች በተሻለ መልኩ የጦር እስረኞች ቢሆኑ መልካም አያያዝ እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል።

ሩሲያም ዩክሬናውያን በአካባቢው ከፍተኛ የበላይነት እንዳላቸው በማመን በሶቪየት ህብረት ዘመን የነበረውን የከተማዋን ስያሜ በመጥቀስ ከክራስንይ ከተማ ወታደሮቿን እያስወጣች መሆኗን ተናግራለች።