በትግራይ ደንጎላት በተባለ ስፍራ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 5 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ  

ታትሟል

በትግራይ ክልል ደንጎላት በተባለ ስፍራ በተፈጸመ የአየር ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውንና 37 ሰዎች መቁሰላቸውን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለህክምና የተወሰዱበት ሆስፒታል ዶክተር ለቢቢሲ ተናገሩ።

ትናንት አርብ ዕለት በሰው አልባ አውሮፕላን ተፈጽሟል የተባለው የአየር ጥቃት ኢላማ ያደረገው ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደንጎላት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

መቀለ የሚገኘው ዋነኛው አይደር ሆስፒታል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ክብሮም ገብረ ሥላሴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የመቁሰል ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ስምንቱ ከፍተኛ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሲሆኑ ሌሎቹም በተለያዩ ደረጃ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በክልሉ ውስጥ ባለው የመገናኛ ዘዴዎች መቋረጥ ምክንያት ቢቢሲ በአካባቢው ካሉ ሌሎች ወገኖች ተፈጸመ ስለተባለው የአየር ጥቃት በተጨማሪ ማረጋገጥ አልቻለም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩን ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ የመከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩምን አስተያየት ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።

ባለፉት ሳምንታት ተመሳሳይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የህወሓት አመራሮች እና የሆስፒታል ምንጮች የተናገሩ ሲሆን ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።

በቅርቡ አዲ ዳዕሮ በተባለ ሥፍራ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ነበር በተባለ ቦታ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞችና ሐኪሞች መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሠራዊቱ የሚፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች በጥንቃቄ የተመረጡ እና ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።

በተጨማሪም ሰላማዊ ሰዎች ለጥቃት ተጋላጭ ሊሆኑ ከሚችሉ ወታደራዊ ኢላማዎች እንዲርቁ ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት አዲ ዳዕሮ ውስጥ የተፈጸመውን የአየር ጥቃት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅታዊ መረጃ ማጣሪ ገጽ በኩል ባወጣው መረጃ “በተመረጡ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ እርምጃ ወስዷል” ሲል ገልጾ ነበር።

በዚህም የአየር ጥቃት ዒላማ የነበረው የህወሓት ኃይሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች እና ተተኳሾች ያሉበት ቦታ ነው ቢልም፣ የትግራይ ኃይሎች አመራሮች ግን በጥቃቱ ዒላማ ተደርጉት ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ብለዋል።

ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት ባለፈው ነሐሴ ወር መልሶ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከሚደረጉት ውጊያዎች በተጨማሪ በተለያዩ ስፍራዎች የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በንግግር ለማስቆም የአፍሪካ ኅብረት ባለፈው ሳምንት ያቀረበውን ጥሪ ሁለቱም ወገኖች መቀበላቸውን አሳውቀዋል።

እሁድ እንደሚጀመር ተገልጾ የነበረው ንግግር በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሌላ ጊዜ ሳይሸጋገር እንደማይቀር ሮይተርስ ዲፒሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን፣ ከአሸማጋዮቹ አንዱ የሆኑት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ደግሞ ይካሄዳል በተባለው ንግግር ላይ ለመገኘት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

እስካሁን የአፍሪካ ኅብረት ንግግሩ በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ ወይም ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።