ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ጦርነት ለምን ያህል ጊዜ መቀጠል ትችላለች?
የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ሰባት ወራት አልፈዋል። በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጫና ቢያሳድርም የቴህራን መሪዎች ግጭቱን ለመግታት የተጣደፉ አይመስልም።
አሜሪካ ለብቻዋ የጦርነቱን አካሄድ መወሰን እንደማትችል ለማሳየት ይፈልጉ ይሆናል።
አሜሪካን በወታደራዊ አቅም፣ በምጣኔ ሃብት እና በፖለቲካ ዋጋ ማስከፈልም ይሻሉ። በዚህ መንገድ ዋሽንግተን የቴህራንን ጥያቄ እንድትቀበል ጫና ማድረግ ይቻላል።
ለመሆኑ ኢራን በዚህ ጦርነት መቀጠል የምትችለው እስከመቼ ነው?
ኢራን ጦርነቱን የማራዘም አቅም አላት?
የኢራን መከላከያ ዘርፍ እና ሚሳዔል ማምረቻዎች በከፊል ጥቃት ደርሶባቸዋል። ነገር ግን ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ በገለልተኛ አካል የወጣ አሐዝ የለም።
ቻተም ሐውስ የባለሙያዎች ቡድን (ቲንክ ታንክ) በቅርቡ ባወጣው ዳሰሳ መሠረት፤ ኢራን አሁን ያላት የሚሳዔል ክምችትን በተመለከተ የተረጋገጠ መረጃ የለም።
ኢራን በጊዜ ሒደት የምትተኩሰው ባለስቲክ ሚሳዔል ቁጥር ቀንሷል። ነገር ግን ጦርነትን የመቀጠል አቅም በሚሳዔል ቁጥር ብቻ አይለካም።
ድሮን እና ክሩዝ ሚሳዔል በቀላሉ ማምረት ይቻላል።
እስካሁን ድረስ የተገደሉ ኮማንደሮች ተተክተዋል። ወታደራዊ ዕዙም ባለበት ነው።
በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር መሐመድ ጋሕዲ "ኢራን ለረዥም ጊዜ የመተኮስ አቅም ይኖራታል። መጠኑ ውስን ቢሆንም እንኳን በሆርሙዝ ወሽመጥ ቀውስ ይፈጥራል" ይላል።
የኢራን ባለሥልጣናት የተራዘመ ግጭት አሜሪካን እንደሚጎዳት ያምናሉ።
የኢራንን ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ማክሸፍ የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ክምችት ላይ መመናመን አስከትሏል።
አንዳንድ የዋሽንግተን ግምገማዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ እነዚህ መሣሪያዎች በፍጥነት የሚተኩ አይደሉም።
መሐመድ "ጦርነቱ በነዳጅ ዋጋ እና በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ያሳደረው ጫና ቴህራን በዋሽንግተን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እና ቅድመ ሁኔታዎችን እንድትቀበል ማድረግ እንደምትችል እንድታምን አድርጓል" ሲል ይገልጻል።
ዲሞክራት መራጮች አሁንም ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋፋቸውን ቢሰጡም አሜሪካውያን ፍጭቱን እንደማይደግፉ የዳሰሳ ጥናቶች ያሳያሉ። ትራምፕ በጦርነቱ ግባቸውን መትተዋል ብለውም አያምኑም።
የቴህራን ስሌት ትክክል ከሆነ፤ ግብ አድርጋ ያስቀመጠችው የአሜሪካ ጦር ማሸነፍ አይደለም።
የተራዘመ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ጦርነት ጫና ለማሳደር ያግዛል።
አሁን ላይ ወታደራዊ ውስንነት ብቻውን ኢራን ጦርነቱን እንድታቆም የሚያስገድዳት አይመስልም።
የኢራን ምጣኔ ሃብት ጦርነቱን መቋቋም ይችላል?
ጦርነቱ ከመጀመሩም በፊት የኢራን ምጣኔ ሃብት በዋጋ ንረት፣ በኢንቨስትመንት ውስንነት እና በገንዘብ ዋጋ ማጣት እየተፈተነ ነበር።
ወርልድ ባንክ እንደሚለው፤ የኢራን ምጣኔ ሃብት በአውሮፓውያኑ ከ2025 እስከ 2026 ባሉት ዓመታት በ2.7 በመቶ ቀንሷል።
ጦርነቱ በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ሌላ ተጽዕኖ ፈጥሯል። የአገሪቱ ስታትስቲክስ ማዕከል ባወጣው መረጃ መሠረት የ12 ወራት የዋጋ ንረት 62 በመቶ ደርሷል።
በተለይም የበለጠ ለጦርነቱ ተጋላጭ በሆነው በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ጫናው በርትቷል።
ለምሳሌ በሞርሞዝጋን ግዛት የዋጋ ንረት 101 በመቶ ሆኗል።
የኢራን የሠራተኞች ሚኒስቴር እንዳለው፤ በጦርነቱ ምክንያት አንድ ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች ሲዘጉ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ሥራ አጥ ሆነዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በ2026 የኢራን ምጣኔ ሃብት 5.4 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል እና የዋጋ ንረት 69 በመቶ እንደሚደርስ ገምቷል።
የጦርነቱ ርዝመት እና በነዳጅ እና ንግድ ዘርፍ የፈጠረው መስተጓጎል ከፍተኛውን ተጽዕኖ አሳድሯል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ ጫና ማሳደሪያም ለጉዳት የሚያጋልጥም ነው።
በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል አሜሪካ በጦርነቱ የምታወጣውን ወጪ ከመጨመር ባሻገር ዓለም አቀፉን የኢነርጂ ዘርፍ ይፈትናል።
አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችው የባሕር እንቅስቃሴ እገዳ የቴህራን የነዳጅ ኤክስፖርትን ይገድባል።
ምጣሄ ሃብታዊ ጫና ለውጥን የሚያመጣ ነው ማለት ግን አይደለም።
መሐመድ እንደሚለው፤ አምባገነን መንግሥታት በከባድ የምጣኔ ሃብት ውስጥ ለዓመታት መቀጠል ይችላሉ።
የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት እና መዋቅራዊ መዋዠቅ የሕዝቡን ደስታ ቢቀማም የቴህራንን ወታደራዊ ፖሊሲ አይለውጥም።
ለውጥ ሊኖር የሚችለው አገር አቀፍ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተነሳ መሆኑን ተንታኙ ያስረዳል።
ጦርነቱ ለምን ያህል ጊዜ ይቀጥላል?
የወደፊቱን በተመለከተ በቴህራን ባለሥልጣናት መካከል ስምምነት የለም።
የፓርላማ አፈ ጉባዔ እና የተደራዳሪ ቡድን መሪ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር አገሪቱ "በሚያዳክም ግጭት" ውስጥ መቀጠል የለባትም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ድርድርን የሚነቅፉ አካላትንም ተችተዋል።
የምክር ቤት አባሉ አሚርሆሴን ሳቤቲ በበኩላቸው አሜሪካ ሁሉንም የኢራን ቅድመ ሁኔታዎች ተቀብላ ስምምነት ቢፈረምም ጦርነቱ አይቀርም ይላሉ።
የቴህራን ባለሥልጣናት ክፍፍል ጦርነት ወይም ሰላምን የሚደግፉ ተብሎ በሁለት መንገድ ብቻ የሚታይ አይደለም።
ጋባሊፍ የኢራንን መብት የማያስጠብቅ ስምምነት እንደማይቀበሉ ይናገራሉ።
በቴህራን አመራሮች መካከል ያለው ልዩነት ትኩረት ያደረገው ለምን ያህል ጊዜ ጫና እያሳደሩ መቀጠል ይቻላል በሚለው ነው።
በየትኛው ነጥብ ላይ ሲደረስ ነው የሚከፈለው ዋጋ ከውጤቱ ያነሰ የሚሆነው? በሚለው ላይም ስምምነት የለም።
ሕዝቡ ምን ያስባል? የሚለውን ለማወቅ በገለልተኛ አካል የተሠራ የዳሰሳ ጥናት የለም።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች ደግሞ አጠቃላይ ሕዝቡን አይወክሉም።
በጀርመን ኢንስቲትዩት ፎር ኢንተርናሽናል ኤንድ ሴክዩሪቲ አፌርስ ባለሙያ እና የኢራን ጉዳዮች ተንታኝ ሐሚድረዛ አዚዚ እንደሚለው፤ ለእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ከፍተኛ ፈተና የሚሆነው የዋጋ ንረት፣ የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት እና በአገሪቱ መሠረተ ልማት ላይ የደረሰው ውድመት ነው።
ከጦርነቱ መውጫ መንገድ
የተራዘመ ጦርነት ኢራን ከቀጣናው አገራት ጋር ያላትን ግንኙነትም ይጎዳል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ኢራን በተለይም ከሳዑዲ አረቢያ እና ከተቀሩትም የባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር ግንኙነቷን ለማደስ እየሞከረች ነው።
በሳዑዲ የሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ኢራን ያደረሰችው ጦርነት ይህንን የሚቀለብስ ይሆናል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ውጥረትን ለማርገብ እና ወደ ድርድር ለመመለስ እየሞከሩ ነው።
ነገር ግን ለኢራን እና አጋር ኃይሎች ጥቃቶች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ሲሰማቸው ቴህራንን ለመገዳደር ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ትብብር ሊያደርጉ ይችላሉ።
በጦርነት ምክንያት ዋሽንግተን ላይ የሚደርስ ጫና ለቴህራን ጠቃሚ የሚሆነው በድርድር ጠረጴዛው ተጽዕኖ ለማሳደር የሚያግዝ ከሆነ ነው።
ኢራን ጦርነቱን እንድታቆም ማድረግ የሚችል ስምምነት ምን እንደሚመስል ወይም እንዴት ከዚህ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ግልጽ አይደለም።
ሐሚድሬዛ እንደሚናገረው፤ ኢራን በጦርነቱ ወቅት ያገኘችው ጫና የማሳደር አቅም በምን መንገድ ወደ ፖለቲካዊ ስምምነት ሊያመራ እንደሚችል የቴህራን ስትራቴጂ በግልጽ አያሳይም።
ቴህራን ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ዘርፍን ማቃወስ እና አሜሪካ እና አጋሮቿ በጦርነቱ የሚያወጡትን ወጪ መጨመር እንደምትችል አሳይታለች።
ነገር ግን ከአሜሪካ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር ለምን ያህል ጊዜ በግጭት ውስጥ መቆየት እንደምትችል ግልጽ አይደለም።
እስካሁን ድረስ ወታደራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ውስንነቶች ኢራን ጦርነቱን እንዳትቀጥል አልገደቡም።
ነገር ግን ጦርነቱ ለረዥም ጊዜ ሲቀጥል፣ የኢራን ቀጣናዊ ግንኙነት የበለጠ እየተበላሸ፣ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከባድ እየሆነ እና የምጣኔ ሃብት ጫናውም እየበረታ መሄዱ አይቀርም።