ሐማስ የለቀቀው ቪዲዮ አሜሪካዊ እና እስራኤላዊ ታጋቾች በጋዛ በሕይወት እንደሚገኙ አሳየ

ታትሟል

ሐማስ ያወጣው ቪዲዮ አንድ አሜሪካዊ እና አንድ እስራኤላዊ ታጋቾች በጋዛ በሕይወት እንደሚገኙ ማረጋገጫ ሆኗል ተባለ።

ቪዲዮ መቼ እንደተቀረጸ የተባለ ነገር ባይኖርም በቪዲዮ ላይ የሚታየው እስራኤላዊው ኦማሪ ሚራን ለ202 ቀናት ተይዞ መቆየቱን ይናገራል። አሜሪካዊው ኪዝ ሲጂል ደግሞ ከሳምንት በፊት የተከበረውን የአይሁዶች በዓል በንግግሩ ስለሚጠቅስ ቪዲዮ በቅርብ የተቀረጸ ስለመሆኑ አመላካች ሆኗል።

ሁለቱም ታጋቾች ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመ ወቅት ነበር ታግተው ወደ ጋዛ የተወሰዱት።

ቪዲዮውን ተከትሎ የታጋቾቹ ቤተሰቦች የእስራኤል መንግሥት ታጋቾቹን ነጻ ለማውጣት ከሐማስ ጋር ድርድር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሐማስ የታጋቾቹን ምስል ያወጣው በእስራኤል እና ሐማስ መካከል አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር እየተደረገ መሆኑ በተገለጸበት ወቅት ነው።

ሁለቱን አካላት እያግባባች ያለችው ግብጽ አደራዳሪዎቿን ወደ እስራኤል መላኳ ተሰምቷል።

ሐማስ እና እስራኤል የሚያደርጉት ድርድር የሚሳካ ከሆነ ዘላቂ ባይሆንም እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ራፋ ለማድረግ ያቀደችውን ወታደራዊ የምድር ዘመቻ አስቁሞ በጋዛ የተያዙ ታጋቾችን ነጻ ያወጣል።

አሜሪካዊው ሲጂል ከባለቤቱ አቪቫ ጋር ነበር የታገተው። ይሁን እንጂ ባለቤቱ አቪቫ ቀደም ባለ ድርድር ነጻ ከወጡት ታጋቾች መካከል አንዷ ናት።

አቪቫ ከእገታ ነጻ ከወጣች ከሳምንታት በኋላ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ባለቤቷ ሲጂል በሕይወት መቆየት ስለመቻሉ ጥርጣሬ እንዳላት ተናግራ ነበር።

ቪዲዮው መውጣቱን ተከትሎ የሲጂል ሴት ልጅ ኢላን “አባቴን ዛሬ በቪዲዮ መመልከቴ ሁላችንም ታጋቾች ነጻ እንዲወጡ ድርድር እንዲደረግ ጥረት ማድረግ እንዳለብን አስገንዝቦኛል” ብላለች።

የኦማሪ ሚራን አባት የሆነው ዳኒ ሚራን ደግሞ ከቪዲዮው መውጣት በኋላ በቴል አቪቭ በተደገረ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ ሆኗል።

ዳኒ ሚራን ልጁ በሕይወት መኖሩን ማወቁ ትልቅ እረፍት እንደሰጠው ተናግሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ መንግሥት ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከዚህ የተሻለ መሥራት አለበት ብሏል።

ሐማስ ከአንድ ሳምንት በፊት እንዲሁ እስራኤላዊ-አሜሪካዊ የሆነው የ23 ዓመቱ ሄርሽ ጎልድበርግ-ፖሊን በሕይወት መኖሩን የሚያሳይ ምስል አውጥቶ ነበር።

በምስሉ ላይ የ23 ዓመቱ ወጣት የግራ እጅ የታችኛው ክፍል ተቆርጦ አሳይቷል። ወጣቱ ጉዳቱ ያጋጠመው ሐማስ መስከረም 26 ድንገተኛ ጥቃቱን በፈጸመ እለት መሆኑም ተገልጿል።

በዚህ ቪዲዮ ላይ የ64 ዓመቱ ሲጅል እና የ46 ዓመቱ ሚራን ታጋቾችን ነጻ ለማውጣት የእስራኤል መንግሥት ከሐማስ ጋር ድርድር እንዲያደርግ ሲጠይቁ ይታያሉ።

ሚራን፤ “በሐማስ ከተያዝኩ 202 ቀናት አልፈዋል። በዚህ ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ ነው። በርካታ ቦምቦች አሉ” ይላል።

እስራኤል እና ሐማስ የሚያደርጉት ድርድር በተለያዩ እክሎች ሳይሰምር ቀርቷል።

ከዚህ ቀደም እስራኤል ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም አድርጋ ቀሪ 40 ታጋቾች ተላልፈው እንዲሰጧት ጠይቃ ነበር። ይሁን እንጂ ሐማስ ይህን ውድቅ አድርጎታል።

ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች የምለቀው እስራኤል የከፈተችብኝ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ቆሞ፣ የእስራኤል ሠራዊት ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ሲወጣ እና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ነው ይላል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ መንግሥት ሐማስን ከምድረ ገጽ አጥፍቼ ታጋቾቹን ነጻ አወጣለሁ ሲል ይደመጣል።

ሐማስ በመስከረም 26ቱ ድንገተኛ ጥቃቱ ከ1ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ገድሎ 250 ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይታወሳል።

በሌላ በኩል እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ በአብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ34ሺህ በላይ ሰዎችን በጋዛ ገድላለች።

ከጥቂት ወራት በፊት እስራኤል እና ሐማስ የደረሱት ስምምነት 105 ታጋቾች ተለቀው ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ነበር።

133 ታጋቾች አሁንም በጋዛ እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ መካከል 30 የሚሆኑ ታጋቾች በሕይወት ላይገኙ ይችላሉ የሚል ግምት አለ።