ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔታንያሁ የፍልስጤምን አገር መሆን እንደሚቃወሙ ለአሜሪካ ገለጹ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ በጋዛ ያለው ግጭት ሲያከትም የፍልስጤምን አገር መሆን እንደሚቃወሙ ለአሜሪካ እንደገለጹ ተናገሩ።
ጋዛ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ጥቃት እንደሚቀጥሉም ኔታንያሁ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
“እስክናሸንፍ፣ ሐማስን እስክናጠፋ፣ እስራኤላውያን ታጋቾችን እስክናስለቅቅ ይቀጥላል። ወራት ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።
በጋዛ 25,000 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል። 85% የጋዛ ነዋሪዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
የእስራኤል አጋር የሆኑት እንደ አሜሪካ ያሉት አገራትና የእስራኤል ተቃዋሚ አገራትም በአካባቢው ሁለት አገራት የሚፈጠሩበት አማራጭ (two-state solution) እንዲተገበር ይገፋፋሉ።
እስራኤልም ፍልስጤምም አገር ሆነው የሚቀጥሉበትን ይህንን አማራጭ እንደማይቀበሉ ነው ኔታንያሁ የተናገሩት።
አማራጩ ደም መፋሰስን የሚያስቆም እንደሆነ ይገለጻል።
ኔታንያሁ ግን ከዮርዳኖስ ባሕር በስተምዕራብ ያለውን አካባቢ እስራኤል መቆጣጠር አለባት ይላሉ።
ይሄ ደግሞ ፍልስጤም ለወደፊት አገር ልትሆን የምትችልበትን ቦታ የሚጠቀልል ነው።
“ይሄ መሆኑ ግድ ነው። የፍልስጤም ሉዓላዊነት ከሚለው ሐሳብ ይቃረናል። ታዲያ ምን ይደረግ? አሜሪካውያን ወዳጆቻችን እውነቱን እንንገራችሁ። የእስራኤልን ደኅንነት የሚነካ ሐሳብ ከመሰንዘር ተቆጠቡ” ብለዋል።
አሜሪካ ግን ጫና ማድረግ ቀጥላለች። አሁን ያለው ግጭት እንዲቆም ትሻለች። ይህም እስራኤል ከምዕራባውያን ወዳጆቿ ጋር ያላት ትብብር እየሳሳ ለመምጣቱ ማሳያ ነው።
በጋዛ እስራኤል እያደረሰች ባለው ጥቃት እየደረሰ ያለውን ቀውስ በመመልከት ግጭቱ እንዲቆም ጫና እየበረታ መጥቷል።
እስራኤል ዒላማ ብቻ እንድትመታና አንድን አካባቢ በስፋት የሚመታ መሣሪያ ከመጠቀም እንድትቆጠብ ዋይት ሀውስ ጫና ለማድረግ እየሞከረ ነው።
እስራኤል ግን ይህንን አልተቀበለችም።
የኔታንያሁን ንግግር ተከትሎ ዋይት ሀውስ ምላሽ ሰጥቷል።
የዋይት ሀውስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቨን እንዳሉት አሜሪካ ሁለት አገራት የሚፈጠሩበትን አማራጭ ለማስተግበር ጥረቷን ትቀጥላለች።
“ጋዛን መልሶ በቁጥጥር ሥር ማዋል አይኖርም” ብለዋል።
ኔታንያሁ የሰጡት አስተያየት አክራሪ ቀኝ ዘመም ደጋፊዎቻቸውን ሲያስደስት፣ በተለያዩ አገራት የሚኖሩና እየደረሰ ያለው ቀውስ የሚረብሻቸውን ዜጎች ግን ያስከፋል።
አብዛኞቹ እስራኤላውያን ቅድሚያ እንዲሰጠው የሚፈልጉት ታጋቾችን ማስለቀቅ ነው።