የቀድሞው የዩናይትድ፣ ቼልሲ እና ማድሪድ አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ከሮማ ተባረሩ

ታትሟል

የጣሊያኑ ክለብ ሮማ ከፖርቹጋላዊው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ጋር መለያየቱን አስታወቀ።

በአውሮፓውያኑ ግንቦት 2021 ሮማን የተረከቡት ጆሴ ሞሪንሆ የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል።

ነገር ግን ዘንድሮ ብዙም ውጤት ያልቀናቸው ሞሪንሆ ባለፈው ሳምንት በከተማ ተቀናቃኛቸው ላዚዮ ከኮፓ ኢታሊያ ዋንጫ ውጪ ሆነዋል።

ሮማ በሴሪ አ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለፈው እሑድ በኤሲ ሚላን 3 - 1 ተረትቷል።

በሚቀጥለው ዓመት በቻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ ከሚያስችለው ነጥብ በአምስት ዝቅ ብሎ የሚገኘው የጣሊያኑ ቡድን፣ ከአነጋጋሪው አሠልጣኝ ጋር ያለውን ውል አቋርጧል።

የ60 ዓመቱ ሞሪንሆን ያሰናበተው ሮማ “በክለባችን ስም ጆሴን ልናመሰግነው እንወዳለን። ከመጣ ጀምሮ ላሳየው ጥልቅ ስሜት እና ቁርጠኝነት ምስጋና እንቸራለን” ብሏል።

የሮማ ባለቤት የሆኑት ዳን እና ራያን ፍሬድኪን በመግለጫቸው “የክለቡን ጥቅም በማስቀደም ለውጥ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን” ብለዋል።

ሞሪንሆ በአውሮፓውያኑ 2022 ሮማን ለአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ድል አብቅተዋል።

ይህ ዋንጫ ለጣሊያኑ ክለብ ከዓመታት በኋላ የተገኘ ጣፋጭ ድል መሆኑን ተከትሎ ሞሪንሆ በደጋፊዎች ዘንድ ትልቅ ሥፍራ ይሰጣቸዋል።

ሮማ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ያነሳው በአውሮፓውያኑ 1961 ነው።

ባለፈው ዓመት ሞሪንሆ ሮማን ይዘው ለአውሮፓ ሊግ ፍፃሜ ቢደርሱም በፍፁም ቅጣት ምት በሲቪያ ተሸንፈዋል።

የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በደካማ አቅም የጀመሩት ሞሪንሆ ከመጀመሪያዎቹ 6 ጨዋታዎች አምስት ነጥብ ብቻ ነው ያገኙት።

ሞሪንሆ ዘንድሮ ከ20 ጨዋታዎች ስምንቱን ሲያሸንፉ በሰባቱ ሽንፈት ቀምሰዋል።

ሞሪንሆ ባለፈው ዓመት የክረምት ዝውውር ወቅት ከሌሎች ክለቦች “ከበድ ያለ ጥያቄ” ቀርቦላቸው ውድቅ እንዳደረጉት ተናግረው ነበር።

ሞሪንሆ በአሠልጣኝነት ዘመናቸው የማሸነፍ ዕድላቸው በመቶኛ ሲሰላ የሮማው [49 በመቶ] ሁለተኛ ዝቅተኛው ነው።

ጆሴ የፖርቶ እና የሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ ሳሉ ነው ከፍተኛውን ውጤት [72 በመቶ] ማስመዝገብ የቻሉት።

ፖርቹጋላዊው አነጋጋሪ አሠልጣኝ ከቤንፊካ ጀምሮ ፖርቶ፣ ቼልሲ፣ ኢንተር ሚላን፣ ሪያል ማድሪድ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሀምን አሠልጥነዋል።

በያዝነው የውድድር ዘመን መቋጫ ኮንትራታቸው ያበቃ የነበረው ሞሪንሆ ቀጣይ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊሄዱ እንደሚችሉ ጭምጭምታዎች መሰማት ጀምረዋል።