ቴክሳስ ስደተኞችን ወደ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ መኖሪያ ቤት ላከች

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

የቴክሳስ ግዛት ስደተኞችን የጫኑ ሁለት አውቶብሶቸ ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ መኖሪያ ቤት ልካለች።

ከስደተኞች ጋር ተያይዞ እየጨመረ በመጣው የፖለቲካ ውዝግብ ምክንያት ሪፐብሊካን የሆኑት የቴክሳስ ግዛት አስተዳዳሪ ሆን ብለው ስደተኞችን እንደላኩ ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው ስደተኞችን የዲሞክራት ፖለቲከኛ ካማላ ሃሪስ ቤት የላኳቸው የስደተኛ ፖሊሲዎች ጥብቅ እንዲሆኑም ለማስታወስ ነው።

እነዚህ ስደተኞች ከቴክሳስ ግዛት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በዚህ ሳምንት ሃሙስ የተላኩ ሲሆን አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተመሳሳይ መልኩ ፍሎሪዳ ወደ ማሳቹስቴስ ደሴት ስደተኞችን ልካለች።

ሁለቱም ግዛቶች በሪፐብሊካን ፖለቲከኞች የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ስደተኞችን ወደ ዲሞክራት ፖለቲከኞች ወደሚተዳደሩ ግዛቶች መላክ እየጨመረ የመጣ ታክቲክ ሆኗል።

አሜሪካና ሜክሲኮ በሚዋሰኑበት ድንበር የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ውጥረቱ እየጨመረ መጥቷል።

በተለይም እንደ ቴክሳስ እና አሪዞና ያሉ ግዛቶች የስደተኛ ህጎችን ማስከበር አልቻሉም ወዳሏቸው ቺካጎ፣ ኒውዮርክ እና ዋሽንግተን ዲሲ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ልከዋል።

የህግ ባለሙያዎች ይህ ስልት በፍርድ ቤት ሊነሳ እንደሚችል ቢገልጹም ሆኖም ውድቅ ሊደረግ የሚችልበትን መሰረት ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ግልጽ አይደለም።

በዋሽንግተን ዲሲ እንዲሁም በማሳቹሴትስ ስለሚላኩ ስደተኞች አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው ከስደተኞች ጋር የሚሰሩ ቡድኖች ተናግረዋል።

በአብዛኛው ከቬንዙዋላ የመጡና ከ75 አስከ 100 የሚደርሱ ስደተኞችን ያሳፈሩ ሁለት አውቶብሶች ወደ ምክትል ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት ደርሰው ሻንጣቸውን ሲያወርዱ ፎክስ ኒውስ አሳይቷል።

በኋላም አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መጥቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳጓጓዛቸው ተዘግቧል።

“ካማላ ሃሪስ ድንበራችን ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ስትል ያለውን ቀውስ ክዳለች” በማለት የቴክሳስ ግዛት አስተዳዳሪ ግሬግ አቦት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

አክለውም “ የባይደን አስተዳደር ስራውን እንዲሰራ እና ድንበሩን እንዲያስጠብቅ ስደተኞችን ወደ ጓሮዋ እየላክን ነው” ብለዋል።