ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጸጋ በላቸውን የጠለፈው የቀድሞ የሐዋሳ ፖሊስ አባል የ16 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደበት
በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችውን ወጣት ጸጋ በላቸው ላይ የጠለፋ እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመው የኋላመብራት ወልደማሪያም በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ።
ውሳኔውን ያስተላለፈው ዛሬ ሐሙስ ታኅሳስ 18፤ 2016 ዓ.ም. የዋለው የሀዋሳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሴቶች እና ህጻናት ችሎት ነው።
ተከሳሹ ሳጅን የኋላመብራቱ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈበት ከሰባት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት አጋማሽ ላይ በፈጸመው ድርጊት ነው።
ይህን ተከትሎ የሀዋሳ ከተማ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት በግለሰቡ ላይ ሁለት ድንጋጌዎች ክስ መመስረቱን ጉዳዩን የሚከታተሉት ዐቃቤ ሕግ አቶ ሮቤል ጌቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጸጋዬ ቱኬ የግል ጠባቂ የነበረው ግለሰብ የመጀመሪያ ክስ በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ ሴትን መጥለፍ በተመከለተ በሰፈረው ድንጋጌ ነው።
ዐቃቤ ሕግ የጠቀሰው የወንጀል ህግ ድንጋጌ፤ “ማንም ሰው አንዲት ሴትን አገባታለሁ በሚል ሀሳብ በኃይል የጠለፈ እንደሆነ” ከሶስት እስከ አስር ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ያትታል።
“ከጠለፋው በኋላ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈጸመ ስለሆነ” በሌላ የወንጀል ድንጋጌ ሁለተኛ ክስ በግለሰቡ ላይ መቅረቡን አቶ ሮቤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህኛው የወንጅል ድንጋጌ መሰረት፤ “የአስገድዶ መድፈሩ ከባድ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳትን ወይም ሞትን ያስከተለ ሲሆን ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ይሆናል” ሲል ይደነግጋል።
ይህ ክስ የቀረበለት የሀዋሳ ከተማ ፍርድ ቤት ባለፈው ታኅሳስ 4፤ 2016 ዓ.ም. ተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።
ከዚህ ውሳኔ ሰባት ቀናት በኋላ ደግሞ የዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽን የቅጣት አስተያየት ተቀብሏል።
አቶ ሮቤል በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረቡት አራት የቅጣት ማክበጃዎች በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። የወንጀሉ አፈጻጸም እና የወንጀሉ ክብደት በቅጣት ማክበጃነት መቅረባቸውን አቶ ሮቤል ገልጸዋል።
አቶ ሮቤል አክለውም፤ “የስራ ኃላፊነቱ ጋር ተያይዞ [የሀዋሳ ከተማ] ከንቲባ የግል ጠባቂ የነበረ ከመሆን አንጻር ያንን መከታ አድርጎ መፈጸሙን አቅርበናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከተከሳሹ ጋር ሌሎች ግብረ አበሮች መኖራቸውን የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ “ወንጀልን ለመፈጸም በተቋቋመ ቡድን ውስጥ የፈጸሙት ነው በሚል አራት የቅጣት ማክበጃዎችን አቅርበን ነበር” ሲሉ አቶ ሮቤል ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሹ ያቀረባቸው ሁለት የቅጣት ማቅለያዎችን ፍርድ ቤቱ መቀበሉን አቶ ሮቤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተከሳሹ ሳጅን የኋላመብራት ያቀረባቸው የቅጣት ማቅለያዎች፤ ከዚህ በፊት ወንጀል ፈጽሞ አለማወቁን እና “ቤተሰብ አስተዳደሪ ነኝ” የሚሉ መሆናቸውን ዐቃቤ ህጉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሁለቱን የቅጣት ማቅለያዎች የተቀበለው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።