በ2022 የሚጣሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮች አምስት ቢሊዮን እንደሆነ አንድ ጥናት አመላከተ

የሞባይል ስልክ

የፎቶው ባለመብት, Eirik Solheim

ታትሟል

በአውሮፓውያኑ 2022 ዓመት 5.3 ቢሊዮን የሞባይል ስልኮች እንደሚጣሉ ኢንተርናሽናል ዌስት ኤሌክትሪካል እና ኤሌክትሮኒክ ኢኩፕመንት ወይም በምህፃረ ቃር ደብልዩ ኢኢኢ የተሰኘው ተቋም አስታወቀ።

በአለም አቀፍ የንግድ መረጃ ላይ የተመሰረተው ይህ ጥናት እየጨመረ የመጣውና የኤሌክትሮኒክ ቆሻሻና በአካባቢ ላይ እየፈጠረ ያለውንም እክል አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

በርካታ ሰዎች አሮጌ የሞባይል ስልኮቻቸውን እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ለኩባንያዎች ከመስጠት ይልቅ እንደሚያስቀምጡ ጥናቱ ጠቁሟል።

ቆሻሻ ተብለው ከሚጣሉ ኤሌክትሮኒክስ ቁሶች በሽቦው ውስጥ ያለው መዳብ በባትሪው ውስጥ ያለው ኮባልት የመሳሰሉ ውድ ማዕድናት ወጥተው እንደገና ጥቅም ላይ ይውላሉ።

“በርካቶች እነዚህ ኢምንት የሚመስሏቸው ቁሶች ዋጋ እንዳላቸውና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስንመለከተው ደግሞ ከፍተኛ መጠን እንደሚኖረው አይገነዘቡም” በማለት የደብልዩ ኢኢኢ ዋና ዳይሬክተር ፓስካል ሌሮይ ተናግረዋል።

በዓለም ዙሪያ ወደ 16 ቢሊዮን የሚጠጉ የሞባይል ስልኮች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን በአውሮፓ ደግሞ አንድ ሦስተኛው በሚባል ሁኔታ ጥቅም የማይሰጡ ስልኮች አሉ።

ተቋሙ በጥናቱ እንደተረዳው በአለም ላይ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች በከፍተኛ መጠን መጨመራቸውን ነው።  ዓለም ከሚገለገልባቸው ከልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ታብሌቶች፣ ኮምፒውተሮች፣ የጂፒኤስ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች ክምቸት በ2030 ወደ 74 ሚሊዮን ቶን እንደሚሆንም ግምቱን አስቀምጧል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኬሚስትሪ ሮያል ሶሳይቲ ከኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎች ማዕድናትን በማውጣት አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት በሚያስተዋውቀው ዘመቻ የዩክሬንን ጦርነት ጨምሮ ዓለም አቀፍ ግጭቶች የብረት አቅርቦት ሰንሰለቶችን አደጋ ላይ እንደሚጥልም አፅንኦት ሰጥቷል።

“እነዚህ መሳሪያዎች በርካታ አዳዲስ የኤሌክትሮኒከል መሳሪያዎችን ለማምረት ያገለግላሉ። ለምሳሌም ያህል የንፋስ ተርባይኖች፣ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች፣ የሶላር መሳሪያዎችን በማምረት ለአረንጓዴ ልማትና ለዝቅተኛ የካርቦን ማህበረሰብ ሽግግር በሚደረገውም ሂደት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ” በማለት የደብልዩ ኢኢኢ ባልደረባ የሆኑት ማግዳሌና ቻሪታኖቪች ይናገራሉ።

ከ17 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለማችን ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች በአግባቡ እንደገና ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት አለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት በሚቀጥለው አመት ይህንን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ግብ አውጥቷል።

"በፍጥነት እየጨመረ ያለና በሰው ጤና እና በአካባቢ ላይ ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ሊይዝ በመያዙም በጣም ውስብስብ ከሆኑ ቆሻሻዎች አንዱ መሆኑንም አሳይ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም ከ20 ሚሊዮን በላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያልሆኑ ነገር ግን የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች እስከ 5.63 ቢሊዮን ፓውንድ የሚገመት ዋጋ ያላቸው በቤቶች ውስጥ እንደተከማቹም የድርጅቱ ጥናት ጠቁሟል።