በጋዛ በእስራኤል ጥቃት ከ60,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

የሚያለቅሱ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከመስከረም 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ከ60,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሰኞ ዕለት የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 60,034 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 18,592 ሕጻናት እና 9,782 ሴቶች ናቸው።

ከማክሰኞ ማለዳ በፊት ባሉት 24 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 112 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 22 ሰዎች እርዳታ ለማግኘት ሲሞክሩ መሞታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የሆስፒታል ምንጮች እና የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደገለፁት በሌሊት እና በማለዳ በመኖሪያ ቤቶች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከተገደሉት መካከል ሴቶች እና ሕጻናት ይገኙበታል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በደቡብ እስራኤል ላይ በፈፀመው ድንገተኛ ጥቃት 1,200 ሰዎች ገድሎ 251 ሰዎችን ካገተ በኋላ በምላሹ እስራኤል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።

ማክሰኞ ጠዋት በማዕከላዊ ኑሴይራት አካባቢ የሚገኘው አል አውዳ ሆስፒታል ለሊቱን በመኖርያ ቤቶች ላይ በደረሱ ጥቃቶች 14 ሴቶች እና 12 ሕጻናትን ጨምሮ 30 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

ከተገደሉት መካከል ብዙዎቹ ዘመዳማቾች መሆናቸው በስም ተዘርዝሮ ተገልጿል።

በካን ዮኒስ የባህር ዳርቻ አል ማዋሲ እስራኤል በተፈናቃዮች መጠለያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን የናስር ሆስፒታል ተናግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በካን ዮኒስ ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

በጋዛ ከተማ እስራኤል የአንድ ቤተሰብ መኖርያ አፓርታማ ላይ በፈፀመችው የሚሳኤል ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል ሲል አል ሺፋ ሆስፒታል ተናግሯል።

ከዚያ በኋላ በተፈፀመ ጥቃት አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገድለዋል።

በሌላ ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ የነፍስ አዳኝ ሠራተኞች ሲረባረቡ ታይተዋል።

አል አውዳ ሆስፒታል በማዕከላዊ ጋዛ የእርዳታ ማከፋፈያ አቅራቢያ በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቢያንስ 14 ሰዎች ሲገደሉ ከ100 በላይ ቆስለዋል ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል " የተካሄደውን ግምገማ ተከትሎ፣ ከሪፖርቶቹ በተቃራኒ ሠራዊቱ በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ ከእርዳታ ማከፋፈያ አጠገብ በወታደሮቹ ተኩስ የተነሳ ስለደረሰው ጉዳት እውቅና የለውም" ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ በኑሴራት "በርካታ የሽብር ዒላማዎችን" መምታቱን እና "በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል" እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጿል።

ቢቢሲ ስለሌሎች ስለተፈጸሙ ጥቃቶች አስተያየት እንዲሰጥ የጠየቀ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።

የእስራኤል ጦር በቴሌግራም ላይ ባወጣው መግለጫ ባለፉት ቀናት በካን ዮኒስ ውስጥ "አደጋ የደቀኑ በርካታ አሸባሪዎችን" እና "የአሸባሪዎችን መሠረተ ልማት እና በርካታ የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ቦታዎችን" ማውደሙን ገልጿል።

በሰሜን ጋዛ ውስጥ "በርካታ አሸባሪዎችን" ማጥፋቱን እና "በምድርም ሆነ ከመሬት በታች ያሉትን የሽብር መሠረተ ልማቶችን" ማውደሙን እና በሰርጡ በርካታ የሽብር ዒላማዎችን መምታቱን ተናግሯል።

ከግንቦት 27 ጀምሮ ከ1,000 በላይ ፍልስጤማውያን ምግብ ለማግኘት ሲሞክሩ በእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

አብዛኞቹ ሟቾች በግንቦት መጨረሻ ስራውን የጀመረው በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን (GHF) እና ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማከፋፈያዎች አቅራቢያ በሚገኙት አካባቢ ነበሩ።

እስራኤል ወታደሮቿ የማስጠንቀቂያ ጥይት መተኮሳቸውን ገልጻ ሆን ብለው ሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደማይተኩሱ ተናግራለች።

የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን የተባበሩት መንግሥታት በሐማስ ከሚመራው የጤና ሚኒስቴር "የውሸት" ቁጥሮችን እየተጠቀመ ነው ሲል ያስተባብላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ማክሰኞ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የቡድኑ ተደራዳሪዎች በጋዛ ረሃብ እያለ ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት እንደሚያቆሙ ለኳታር እና ግብፅ አሸምጋዮች አሳውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት እስራኤል እና አሜሪካ ከድርድር ወጥተው መሄዳቸውን ማሳወቃቸው ይታወቃል።

አሜሪካ ሐማስ በቅን ልቦና እየተደራደረ አይደለም ስትል ኔታንያሁ በበኩላቸው አሁንም በጋዛ ታግተው የሚገኙትን ለመመለስ "ያሉ አማራጮችን እያጤንን ነው" ብለዋል።

በድርድሩ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ሰፊ አለመግባባቶች ታይተዋል።

እነዚህም የእስራኤል ወታደሮችን መውጣት፣ የእርዳታ ክፍፍል እና ጦርነትን በዘላቂነት ማቆም ናቸው።

ማክሰኞ ዕለት በጋዛ የረሃብ መስፋፋት ላይ ከባድ ማስጠንቀቂያዎች መውጣታቸውን ቀጥለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፉ የዓለም የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች በጋዛ ሰርጥ የከፋ ረሃብ "በአሁኑ ጊዜ እየደረሰ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል ።

እስራኤል በጋዛ ላይ ለደረሰው ሰብዓዊ አደጋ ተጠያቂ አይደለሁም በማለት ወደ ጋዛ በሚገባው እርዳታ ላይ ገደቦችን እንደማትጥል ትናገራለች።

ይህ ግን የቅርብ አጋሮቿ በሆኑት አውሮፓ ወይንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በጋዛ ውስጥ በሚሰሩ ሌሎች ኤጀንሲዎች ተቀባይነት አላገኘም።

እሁድ ዕለት ወደ ጋዛ የሚገቡትን እርዳታዎች በሙሉ የምትቆጣጠረው እስራኤል የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በየቀኑ የ10 ሰዓት "ስልታዊ ፋታ" መጀመሯን ያሳወቀች ሲሆን ለእርዳታ ተሽከርካሪዎች "ደህንነታቸው የተጠበቁ መንገዶች" መከፈታቸውን ገልጻለች።

ስልታዊ ፋታው በሦስት አካባቢዎች ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን፣ በጋዛ ሰርጥ የተለያዩ አካባቢዎች ለሊቱን የአየር ጥቃቶች ቀጥለዋል።

እስራኤል ለጋዛ ነዋሪዎች ከአውሮፕላን እርዳታ እንዲጣል መፍቀዷን ስታሳውቅ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ይህ እርምጃ ውጤታማ ያልሆነ እና አደገኛ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

እስራኤል የሐማስ የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን ሪፖርት ከሟቾቹ መካከል ምን ያህሉ የፍልስጤም የታጠቁ ቡድኖች አባላት እንደሆኑ አይለይም ስትል ተችታለች።

የእስራኤል ጦር በዓመቱ መጀመሪያ ላይ 20,000 የሐማስ እና የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ አባላት በጦርነቱ ወቅት መገደላቸውን አስታውቋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የወታደራዊ ኃይሉ ዋና አዛዥ ባለፉት ሳምንታት ከ1,300 በላይ "አሸባሪዎችን" መምታቱን ተናግሯል።

ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በእስራኤል ወደ ጋዛ ገብተው እንዳየዘግቡ በመከልከላቸው ከሁለቱም ወገን ያለውን መረጃ ማረጋገጥ አልቻሉም።