ኤርትራውያን 'ስልታዊ' የመብቶች ጥሰት ይፈጸምባቸዋል- የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ለሦስት አስር ዓመታት በሥልጣን ላይ በቆዩት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራዊያን ከፍተኛ የመብት ጥሰት እንደሚደርስባቸው የተባበሩት መንግሥታት ልዩ የሰብዓዊ መብት ተከታታይ ራፖርተር አስታወቀ።

በአፍሪካ ቀንድ ወደ 3.5 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ኤርትራ በተለያዩ አካላት የ"የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ" በሚል ቅጽል ስም ትጠራለች።

ለተከታታይ ዓመታት በዓለም ላይ ካሉ አገራት አንጻር በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል።

እንደ ረፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ መረጃ ኤርትራ በፕሬስ ነጻነት ረገድ ከዓለም አገራት በመጨረሻው ተርታ ላይ ትገኛለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2022 ባወጣው የሰብዓዊ ልማት ደረጃ ኤርትራ ከ183 አገራት መካከል 175ኛ ሆናለች።

የኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ የሰብዓዊ መብት ተከታታይ ራፖርተር ሞሐመድ አብደልሰላም ባቢከር ሰኞ በጄኔቫ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ በኤርትራ የሚካሄዱት የሰብአዊ መብተት "ጥሰቶች ስልታዊ ናቸው፤ የተጠያቂነት አስፈላጊነት እጅግ በጣም አጣዳፊ ነው" ብለዋል።

በአንድ ፓርቲ ሥር የምትመራው ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘች ጊዜ አንስቶ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ ተቃውሞን በኃይል በማፈን፣ ተቃዋሚዎችን ያለፍርድ በማሰር እና በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በማቆየት ይከሰሳሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የኤርትራን ብሔራዊ አገልግሎት ሥርዓት ኤርትራውያንን ለዕድሜ ልክ ውትድርና ወይም ለግዳጅ ሥራ የሚዳረግ መሆኑን በመጥቀስ ከባርነት ጋር ያመሳስለዋል።

ወደ ኤርትራ እንዳይገቡ የተከለከሉት ባቢከር "ያለ ምንም ክስ ወይም ፍርድ ለአስርት ዓመታት ታስረው ስላሉበት ሁኔታ ምንም ተሰምቶ የማያውቁ ሰዎች ስማችሁ መነገር ይቀጥላል" ብለዋል።

በተባባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ተወካይ የሆኑት ሐብቶም ዘርዓይ ሪፖርቱን "ግልጽነት እና ሚዛናዊነት የጎደለው" በማለት ተችተዋል።

ልዩ ራፖርተር በኤርትራ ላይ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ሪፖርት እንደ ካሁን ቀደሙ ሁሉ "ባልተረጋገጡ መረጃዎች" እና "ማንነታቸው ባልታወቁ ምንጮች ላይ የተመሠረተ"፣ "ግልጽነትና ሚዛናዊነት የጎደለው " በማለት አጣጥለውታል።

ኤርትራ፣ የልዩ ራፖርተሩ ሪፖርት የተለያዩ የመንግሥታቱ ድርጅቶች በኤርትራ ዙሪያ ከሚያወጧቸው ሪፖርቶች ጋር የሚቃረን መሆኑንም ገልጣለች።

ኤርትራ ለዓመታት በሰብአዊ መብት አያያዟ በአውሮፓ እና በሌሎች ምዕራባውያን አገራት ስትተች ቆይታለች።

ኤርትራ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች በሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በግድጃ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ምክንያት በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲሰነዘርባት ቆይታለች።