ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩሲያ ለአሜሪካ ሲሰልል ነበር የተባለ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ በይፋ ክስ ቀረበበት
አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኢቫን ገርሽኮቪች ላይ በይፋ ክስ መቅረቡን የሩሲያ ሚዲያዎች ዘገቡ።
ጋዜጠኛው ሩሲያ ውስጥ ለዎልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ወኪል ሆኖ ሲሠራ ነበር።
ይሁንና የሩሲያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ይህን አሜሪካዊ ጋዜጠኛ በስለላ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ሳለ እጅ ከፍንጅ ይዘነዋል ይላል።
አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኢቫን ገርሽ ኮቪች በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው ባለፈው ሳምንት ነበር።
ምንም እንኳ ሞስኮ አሜሪካዊውን የያዝኩት እጅ ከፍንጅ ነው ብትልም ጋዜጠኛው ግን የተመሰረተብኝ ክስ የፈጠራ ነው ብሏል።
ቀጣሪው ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኛችን ያለምንም ማመንታት አሁኑን ይለቀቅ ሲል በይፋ ጠይቋል።
የ31 ዓመቱ ጋዜጠኛ ገርሽኮቪች በሞስኮ ለውጭ ሚዲያ ወኪል ሆነው በሚሠሩ ጋዜጠኞች ዘንድ በብርታቱ የሚታወቅ ባለሙያ ነው።
በሩሲያ የቢቢሲ አርታኢ ሰቲቭ ሮሰንበርግ ጋዜጠኛውን “በሙያው የታነጸ” ሲል ይገልጸዋል።
ዋይት ሐውስ የርሱን መታሰር በብርቱ ያወገዘ ሲሆን በርካታ ሴናተሮችም ዜጋቸው እንዲለቀቅ እየወተወቱ ነው።
ሪፐብሊካኑ ጎምቱ እንደራሴ ሚች መክኔል እና የዲሞክራቱ አቻቸው ቸክ ሹመር በጋራ በሰጡት መግለጫ “ጋዜጠኝነት በፍጹም ወንጀል አይደለም፤ እርሱ ላይ የተመሠረተበት ደንበኛ የፈጠራ ክስ ነው፤ ሩሲያ አሁኑኑ እንድትፈታው እንጠይቃለን” ብለዋል።
እስሩን ተከትሎ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛውን ለመጎብኘት እንዲፈቀድላቸው የጠየቁ ሲሆን የሩሲያ መንግሥት ግን ለጊዜው ያን አልፈቀደም። ይሁንና በጠበቆቹ እንዲጎበኝ ሆኗል።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ ጋዜጠኛው እንዲጎበኝ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ገልጾ ይሁንና ሩሲያ ላይ ጫና በመፍጠር አንድን ሰላይ ለማስፈታት የሚደረገው ሙከራ 'ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው' ብሏል።
ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኛችን ባለፈው ረቡዕ ከምሥራቅ ሞስኮ 1600 ኪሎ ሜትር በምትርቀው የካተሪንበርግ ከተማ ሥራ ላይ ሳለ ከደወለልን በኋላ ነው ደብዛው የጠፋብን ይላል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ጋዜጠኛውን የግል ሾፌሩ አንድ ሬስቶራንት ካደረሰው በኋላ ስልኩ እንደተቋረጠና ከዚያ በኋላ በቁጥጥር ሥር ሊውል እንደቻለ ተናግረዋል።
የሩሲያ ደኅንነት እንደሚለው ደግሞ ይህ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሕገ ወጥ ሥራ ሲሠራ እንደነበረና በአሜሪካ የተሰጠውን የስለላ ተልእኮ ሊፈጽም ሲል እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ ይገልጻሉ።
የአገር ምሥጢር የሆኑ መረጃዎችን ከሩሲያ መከላከያ ኢንተርፕራይዝ ሲለቅም ነበር ብለዋል።
ትናንት ዐርብ ጋዜጠኛው በሞስኮ ሌፍሮቶፍ አካባቢ ምድብ ችሎት የቀረበ ሲሆን እስከ ግንቦት መጨረሻ እስር ቤት ቆይቶ ምርመራው እንዲቀጥል ትእዛዝ ተሰጥቶበታል።
አንድ በስለላ ተግባር የተሰማራ ሰው በሩሲያ ሕግ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ እስከ 20 ዓመት ጽኑ እስር ይቀጣል።