የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ታጣቂዎች በሠራተኛው ላይ የፈፀሙትን ግድያ አወገዘ

ታትሟል

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ታጣቂዎች ጥቅምት 18፣ 2015 ዓ.ም የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ የአምቡላንስ አሽከርካሪ ሠራተኛው ላይ የፈፀሙትን ግድያ አወገዘ።

ማኅበሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ በሠራተኛው ሞት ማዘኑን ገልጾ፣ ታጣቂ ኃይሎች ከመሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ተማጽኗል።

የ40 ዓመቱ የአምቡላንስ አሽከርካሪ መንግሥት ምንይል፣በምዕራብ ደንቢያ ሰብዓዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደነበር ማኅበሩ አስታውቋል።

አሽከርካሪው በሰብዓዊ ሥራ ላይ ወልቃይት አዲ ረመጽ ተመድቦ ይሰራ የነበረ ሲሆን በትግራይ ክልል አድዋ ተሰማርተው በግጭት የተጎዱ ሰዎችን በማገዝ ላይ ከነበሩ ሁለት አምቡላንሶች አንዱን ያሽከረክር እንደነበርም ማኅበሩ ጠቅሷል።

የሁለት ልጆች አባት የነበረው አሽከርካሪው በታጣቂዎቹ የተገደለውም ከአድዋ ወደ ወልቃይት አዲ ረመጽ ሆስፒታል ቁስለኞችን ለማድረስ እየሄደ ባለበት ወቅት ነው ብሏል።

ማኅበሩ በአምቡላንሱ ውስጥ የያዛቸው ቁስለኞችም ጭምር መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ ግን አልጠቀሰም።

የጥቃቱ ዓላማ ምን እንደነበር እና ስለ ታጣቂዎቹ ማንነት ማኅበሩ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በሚያከናውናቸው የሰብዓዊ ሥራዎች ጥቃት ተፈፅሞብኛል ሲል ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በባለፈው የካቲት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ሁለት አምቡላንሶች እንደተወሰዱበት የማኅበሩ የዲፕሎማሲ እና የግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ሰለሞን ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ ማኅበሩ ለሰብዓዊ አገልግሎት የሚጠቀምባቸው ሁለቱ አምቡላንሶች በግዳጅ የተወሰዱት በሥራ ላይ እያሉ ነበር። አምቡላንሶቹ በማን እንደተወሰዱ? ለምን እንደተወሰዱ ግን ማኅበሩ ዝርዝር መረጃ እንደሌለው በወቅቱ ገልጸው ነበር።

ሁለት ዓመት ገደማ በሆነው የሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞም የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በሠራተኞቻቸው ላይና ለሰብዓዊ ሥራ በሚገለገሉባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲሁም በእርዳታ ቁሳቁሶች ላይ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው በተለያየ ጊዜ ሲገልጹ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሠራተኛውን መገደል ተከትሎ በማኅበራዊ ገጹ ባወጣው የሐዘን መግለጫ በሰብዓዊ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችና በጎ ፈቃደኞች ተንቀሳቅሰው መስራት እንዲችሉ ታጣቂ ኃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተማጽኖውን አቅርቧል።

በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት በቅርቡ የተገደለውን የዓለም አቀፍ ሬስኪው ኮሚቴ ባልደረባ ጨምሮ  በድምሩ 26 የሰብአዊ ድጋፍ ሠራተኞች መገደላቸውን ተናግረዋል።