ዋይት ሃውስ አቅራቢያ የወደቀ መብረቅ አራት ሰዎች ክፉኛ አቆሰለ

የፖሊስ መኪና

የፎቶው ባለመብት, DC FIRE & EMS

ታትሟል

ዋይት ሃውስ አቅራቢያ የወደቀው መብረቅ አራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰ።

የአካባቢው የድንገተኛ አደጋዎች ባለስልጣናት እንዳሉት በመብረቁ የተመቱት ሁለት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች ዋይት ሃውስ አቅራቢያ ባለ ፓርክ ውስጥ ሳሉ ነበር።

ፓርኩ ለአሜሪካ የፕሬዝዳንት መኖሪያ ካለው ቅርበት የተነሳ ተጎጂዎችን ለመርዳት ቀድመው በስፍራው ከደረሱት መካከል የደህንነት አባላት እንደነበሩበት ተገልጿል።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ማንነት እስካሁን አልተገለጠም።

ሐሙስ አመሻሽ አራቱን ሰዎች የመታው የመብረቅ አደጋ የደረሰው የዋይት ሃውስ አጥር አጠገብ ካለ ዛፍ ጎን ነው።

የዋሽንግተን ዲሲ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ በሰጠው መግለጫ “አራቱም ከከባድ እስከ ለሕይወት አስጊ የሆነ ጉዳት አስተናግደዋል። አራቱንም በፍጥነት አካባቢው ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ተወስደዋል" ብሏል።

ሰዎቹ መብረቁ ከመከሰቱ በፊት ይተዋወቁ እንደሆነ እና ምን ይሠሩ እንደነበር ባለሥልጣናቱ እስካሁን ማወቅ አልቻሉም።

አደጋውን ተከትሎ የፓርኩ የተወሰነ ክፍል ተዘግቶ የቆየ ሲሆን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ባልደረቦች በቦታው ተገኝተዋል።

የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ትንበያ ተቋም ሐሙስ አመሻሽ በአካባቢው ነጎድጓድ እንደሚኖር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።